አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው። (ገላትያ 2፥20)
እምነት እግዚአብሔር በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ ከሚሰጠን ጸጋ ጋር ፍጹም ተስማሚ ነው። ከጸጋ ነፃ እና በቂ መሆን ጋር አብሮ ይሄዳል። እንዲሁም ወደ ከበረው የእግዚአብሔር ታማኝነት ትኩረትን ይስባል።
ከዚህ የምንማረው አንድ ነገር፣ “የሚያጸድቀው እምነት” እና “የሚቀድሰው እምነት” ሁለት የተለያዩ የእምነት ዓይነቶች አለመሆናቸው ነው። በቀላሉ “መቀደስ” ማለት መለየት ወይም ክርስቶስን ወደ መምሰል መለወጥ ማለት ነው። ይህም የሚሆነው በጸጋ ነው።
ስለዚህ፣ በጸጋ ከሆነ፣ በእምነትም በኩል መሆን አለበት። ምክንያቱም እምነት ከጸጋ ጋር የምንቆራኝበት እና የመታዘዝን ኃይል የምንቀበልበት የነፍሳችን ተግባር ነው። ይህም ጸጋን በሰው ትምክህት ከመሻር ይጠብቀዋል።
ጳውሎስ ይህንን በእምነት እና በቅድስና መካከል ያለውን ግንኙነት በገላትያ 2፥20 ላይ በግልጽ ያስቀምጠዋል፦ “የምኖረው . . . ባለኝ እምነት ነው”። ቅድስና በመንፈስ እና በእምነት የሚሆን ነገር ነው። በሌላ አነጋገር፣ በጸጋ እና በእምነት እንደማለት ነው። ምክንያቱም መንፈሱ “የጸጋ መንፈስ” ነው (ዕብራውያን 10፥29)። እግዚአብሔር እኛን የሚቀድሰን በመንፈሱ ነው። መንፈሱ ግን የሚሰራው በወንጌል ላይ ባለን እምነት አማካኝነት ነው።
የሚያጸድቀው እምነት ራሱ የሚቀድሰው እምነት የሆነበት ቀላል ምክንያት፣ ጽደቅም ሆነ ቅድስና የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ጸጋ ሥራዎች መሆናቸው ነው። ከጸጋ ጋር የሚስማማው ደግሞ እምነት ብቻ ነው። ጽደቅ እና ቅድስና አንድ ዓይነት ሥራዎች አይደሉም። መጽደቅ ማለት ጻድቅ ሆኖ መቆጠር ማለት ሲሆን፤ መቀደስ ደግሞ ጽድቅን መቀበል ማለት ነው። ነገር ግን ሁለቱም የጸጋ ሥራዎች ናቸው። ቅድስና እና ጽደቅ “በጸጋ ላይ ጸጋ” የመብዛቱ ማሳያ ናቸው (ዮሐንስ 1፥16)።
ለእግዚአብሔር ነጻ ጸጋ ከሰው የሚጠበቀው ምላሽ እምነት ነው። እናም ጽደቅ እና ቅድስና በእርግጥ የጸጋ ሥራዎች ከሆኑ፣ ሁለቱም የሚገኙት በእምነት በኩል ነው ማለት ነው።