ከጥንት ጀምሮ፣ በተስፋ ለሚጠባበቁት የሚደርስላቸው፣ እንደ አንተ ያለውን አምላክ ያየ ዐይን፣ ያደመጠ ጆሮ ፈጽሞ አልነበረም። (ኢሳይያስ 64፥4)
እግዚአብሔር ለእኔ ብሎ በሚሠራው ሥራ በኩል አምላክነቱን ለማሳየት መውደዱን የመሰለ ልቤን የሚማርክ እውነት የለም። ይህ ለእኔ ብሎ የሚሠራው ሥራ፣ ለእርሱ ብዬ ለምሠራው ሥራ የሁልጊዜ መሠረት እና ምክንያት ነው።
በመጀመሪያ፣ “እግዚአብሔር ለእኛ ይሠራልናል” ማለት ንቀት ወይም እርሱን ማሳነስ ሊመስል ይችላል። ይህ ዐይነት ስሜት የሚነሣው እግዚአብሔር ሥራ አጥ፣ እኛ ደግሞ ስራ ቀጣሪ ነን ከሚል ዕሳቤ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ለእኛ እየሠራ ነው ሲል ይህንን ዐይነት ዕሳቤ እየተናገረ አይደለም። ኢሳይያስም፣ “በተስፋ ለሚጠባበቁት የሚደርስላቸው” ብሎ ሲናገር ይህ ዐይነት ዕሳቤ አእምሮው ውስጥ በፍጹም አልነበረም።
“እግዚአብሔር ለእኛ ይሠራልናል” ስንል ጉልበት የሚያስፈልገን ደካማ ሰዎች መሆናችንን፣ በዕዳ ውስጥ ተዘፈቀን ቤዛን የምንጠባበቅ፣ ጠቢብ የሆነ ሰው የሚያሻን ሕፃናት እና ጠባቂ የሚያስፈልገን የጠፋን ፍጥረቶች መሆናችንን መናገራችን ነው።
“እግዚአብሔር ለእኔ ይሠራልኛል” ማለት እኔ ልሠራው አልችልም እርዳታው ያስፈልገኛል ማለት ነው።
ታዲያ ይህ እኔን ሳይሆን እግዚአብሔርን ያከብረዋል። ቸሩ እግዚአብሔር ክብርን ያገኛል፤ ምስጋናም ለኅያሉ ይሆናል።
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ለእናንተ ስለ መሥራቱ የሚናገረውን ተመልከቱ። እናም የራሳችሁን ቀንበር ከመሸከም ነፃ ውጡ። ሥራውን ለእርሱ አሳልፋችሁ ስጡ።
- “በተስፋ ለሚጠባበቁት የሚደርስላቸው፣ እንደ አንተ ያለውን አምላክ ያየ ዐይን፣ ያደመጠ ጆሮ ፈጽሞ አልነበረም” (ኢሳይያስ 64፥4)።
- “እርሱ ለሰዎች ሁሉ ሕይወትንና እስትንፋስን እንዲሁም ሌላውንም ነገር ሁሉ የሚሰጥ ስለ ሆነ፣ የሚጐድለው ነገር ባለመኖሩ በሰው እጅ አይገለገልም” (ሐዋርያት ሥራ 17፥25)።
- “የሰው ልጅ ሊያገለግልና ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ መጣ እንጂ ሊገለገል አልመጣምና” (ማርቆስ 10፥45)።
- “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉና” (2ኛ ዜና መዋዕል 16፥9)።
- “ብራብ ለአንተ አልነግርህም… በመከራ ጊዜ ወደ እኔ ጩህ፤ አድንሃለሁ፤ አንተም ታከብረኛለህ” (መዝሙር 50፥12፣ 15)።
- “እስከ ሽምግልናችሁ፣ እስከ ሽበትም፣ የምሸከማችሁ እኔ ነኝ፤ እኔው ነኝ። ሠርቻችኋለሁ፤ እሸከማችኋለሁ፤ እደግፋችኋለሁ፤ አድናችኋለሁ” (ኢሳይያስ 46፥4)።
- “እንዲያውም ከሁሉም በላይ በትጋት ሠርቻለሁ፤ ዳሩ ግን እኔ ሳልሆን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው” (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥10)።
- “እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፣ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ” (መዝሙር 127፥1)።
- “ከእናንተ ማንም የሚናገር ቢኖር እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢኖር እግዚአብሔር በሚሰጠው ብርታት ያገልግል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንዲከብር ነው” (1ኛ ጴጥሮስ 4፥11)።
- “የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ እንደ በጎ ፈቃዱ መፈለግንና ማድረግን በእናንተ ውስጥ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና” (ፊልጵስዩስ 2፥12-13)።
- “እኔ ተከልሁ፤ አጵሎስ ውሃ አጠጣ፤ ያሳደገው ግን እግዚአብሔር ነው” (1ኛ ቆሮንቶስ 3፥6)።