ሁሉንም እንገዛለን | ጥር 22

“እኔ ድል ነሥቼ ከአባቴ ጋር በእርሱ ዙፋን ላይ እንደ ተቀመጥሁ፣ ድል የሚነሣውንም ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ።” (ራእይ 3፥21)

ኢየሱስ ይህንን ለሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን ሲናገር ምን እያለ ነው?

የእውነት ከኢየሱስ ጋር በዙፋኑ ላይ መቀመጥ ምን ይመስላል?

ይህ የተስፋ ቃል የተገባው በሕመምና በሚያባብል የኃጢአት ደስታ መካከል በእምነት እስከመጨረሻው በመጽናት ድል ለሚነሣ ሁሉ ነው (1ኛ ዮሐንስ 5፥4)። ስለዚህ እውነተኛ የኢየሱስ አማኝ ከሆናችሁ፣ በእግዚአብሔር አብ ዙፋን ላይ በተቀመጠው በእግዚአብሔር ወልድ ዙፋን ላይ ትቀመጣላችሁ።

“የእግዚአብሔር ዙፋን” ስል አጽናፈ ዓለምን የመግዛት መብትና ሥልጣንን ለማመልከት ነው። ኢየሱስ የተቀመጠው በዚያ ነው። ጳውሎስም “ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ ሥር እስከሚያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና” ይላል (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥25)። ስለዚህ ኢየሱስ “ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ” ሲል፣ ሁሉን ነገር መግዛትን እንደምንካፈል ቃሉን እየሰጠን ነው።

ጳውሎስ በኤፌሶን 1፥22-23 እያለ ያለው ይህንን ይሆን? “እግዚአብሔርም ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዛለት፤ በቤተ ክርስቲያንም፣ በማንኛውም ነገር ላይ ራስ አድርጎ ሾመው። እርሷም ሁሉን ነገር በሁሉም ረገድ የሚሞላው፣ የእርሱ ሙላት የሆነች አካሉ ናት።”

ቤተ ክርስቲያን የሆንን እኛ፣ “ሁሉን ነገር በሁሉም ረገድ የሚሞላው፣ የእርሱ ሙላት” ነን። ይህ ምን ማለት ነው? አጽናፈ ዓለሙ በጌታ ክብር ይሞላል ማለት ነው (ዘኁልቁ 14፥21)። ይህም ክብር የሚገለጥበት አንዱ መንገድ በሙላት ሁሉን መግዛቱ እና የሚቃረነው የሌለ መሆኑ ነው።

ስለዚህ ኤፌሶን 1፥23 ኢየሱስ አጽናፈ ዓለሙን በእኛ በኩል በክብሩ ግዛት ይሞላል እያለን ነው። አገዛዙን በመካፈል ውስጥ እኛም ደግሞ የአገዛዙ ሙላት ነን። በእርሱ ኃይል፣ ለስልጣኑ በመገዛት፣ እርሱን ወክለን እንገዛለን። በዙፋኑ ከእርሱ ጋር እንቀመጣለን።

ማናችንም ግን ይህ እውነት ሊሰማን በሚገባው መጠን አይሰማንም። ለዚህ ነው ጳውሎስ፣ “በእርሱ የተጠራችሁለት ተስፋ፣ ይህም በቅዱሳኑ ዘንድ ያለውን ክቡር የሆነውን የርስቱን ባለጠግነት ምን እንደሆነ ታውቁ ዘንድ የልባችሁ ዐይኖች እንዲበሩ” ብሎ የሚጸልየው (ኤፌሶን 1፥18)።