“ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ አሁን የሆንሁትን ሆኛለሁ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋ ከንቱ አልሆነም፤ እንዲያውም ከሁሉም በላይ በትጋት ሠርቻለሁ፤ ዳሩ ግን እኔ ሳልሆን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው።” (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥10)
ጳውሎስ “ከሁሉም በላይ በትጋት ሠርቻለሁ” ማለቱን በተሳሳተ መንገድ ሰዎች ሊረዱት እንደሚችሉ በማሰብ፣ “ዳሩ ግን እኔ ሳልሆን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው” የሚለውን ጨምሯል።
ጳውሎስ ያለፈውን ጸጋ ለማመስገን የቀድሞ ታዛዥነቱን ወደኃላ አይመለከትም። ይልቁንስ በየጊዜው ያለውን፣ ዘወትር የሚገለጠውን ጸጋ ይመለከታል። በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል መሠረት በችግር ጊዜ ሁሉ በሚያገኘው የእግዚአብሔር ጸጋ ላይ ይደገፋል። ክርስቶስን ለመታዘዝ ባለ የጳውሎስ እያንዳንዱ ፍላጎትና እና ጥረት ሁሉ፣ ጸጋው ደግሞ የዚህን ፍላጎትና ጥረት ፍሬ ለማፍራት አብሮ ይሠራል። ጳውሎስ ሥራውን ሁሉ የሚያከናውነው፣ ባለፈው ጊዜ ስለተሰጠው ጸጋ በማመስገን ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን በየጊዜው በሚሰጠው ጸጋ ላይ በመደገፍ ነው። ጳውሎስ በየጊዜው የሚሰጠው የእግዚአብሔር ጸጋ ለሚሠራው ሥራ ወሳኝ ምክንያት መሆኑ ላይ አጽንዖት መስጠት ፈልጓል።
በርግጥ ግን ያንን ብሏል? የእግዚአብሔር ጸጋ ከጳውሎስ ጋር መሥራቱን ብቻ ነው የሚናገረው? በፍጹም፣ ሌላም ተጨማሪ ነገር ይናገራል፤ “ዳሩ ግን እኔ ሳልሆን” ከሚሉት ቃላት ጋር ልንስማማ ይገባል። ጳውሎስ የዚህ ሥራ ዋነኛ አድራጊ እርሱ አለመሆኑን ግልጽ በማድረግ በየጊዜው የሚሰጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ ከፍ ለማድረግ ፈልጓል።
ቢሆንም እርሱ የዚህ ሥራ አድራጊ ነው፤ “እንዲያውም ከሁሉም በላይ በትጋት ሠርቻለሁ” ይላል፤ በትጋትም ሠርቷል። ነገር ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው ይላል።
የዚህ ጥቅስ ክፍሎች በሙሉ አንድ ላይ እንዲቆሙ ብናደርግ መጨረሻው ይህ ነው፤ የጳውሎስን ሥራ የሚሠራው ጸጋው ነው። ሥራውን የሚሠራው ጳውሎስ እንደመሆኑ፣ ጸጋው ወሳኝ የሆነበት መንገድ የጳውሎስን ሥራ ማስቻል ነው።
ጳውሎስ በእያንዳንዱ ቀን የአገልግሎቱን ሸክም ሲጋፈጠው፣ አንገቱን ደፍቶ፣ ለዚያ ቀን ሥራ ወደፊት ጸጋ ካልተሰጠው፣ ሊሠራው እንደማይችል ነው እየተናዘዘ ያለው። ምናልባትም ክርስቶስ የተናገረውን እያሰበ ይሆናል፤ “ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና” ብሏል (ዮሐንስ 15፥5)። ስለዚህ በየዕለቱ ለሚሰጠው ጸጋ በመጸለይና ይህንንም ኃይል እንደሚያገኝ በጌታው ቃል ታምኗል። “አምላኬም እንደ ታላቅ ባለጠግነቱ መጠን የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ይሞላባችኋል” (ፊልጵስዩስ 4፥19)። ይህንን አመነ፤ ከዚያም በሙሉ ኃይሉ አደረገ።