ስለ እናንተ በምንጸልይበት ጊዜ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እናመሰግናለን፤ ምክንያቱም በክርስቶስ ኢየሱስ ስላላችሁ እምነትና ለቅዱሳን ሁሉ ስላላችሁ ፍቅር ሰምተናል፤ ይህም የሆነው በሰማይ ተዘጋጅቶ ከተቀመጠላችሁ ተስፋ የተነሣ ነው። (ቈላስይስ 1፥3-5)
የዛሬይቷ ቤተ ክርስቲያን ችግር በመንግሥተ ሰማይ ፍቅር የወደቁ ምእምናን መብዛታቸው አይደለም። ከዓለም ሸሽተው ግማሽ ቀናቸውን ቃሉን በማንበብ፣ ግማሹን ደግሞ በእግዚአብሔር ያላቸውን ደስታ በዝማሬ በመግለጽ የሚያሳልፉ ክርስቲያኖች መኖራቸውም አይደለም። እየሆነ ያለው ይህ አይደለም! የእግዚአብሔር ሰዎች ለእርሱ ያላቸው ፍቅር ከመብዛቱ የተነሣ ግማሽ ቀናቸውን ከቃሉ ጋር ሲያሳልፉ መዋላቸው አይደለም ችግር እየሆነ ያለው።
ችግሩ ክርስቲያን ነን ባዮች በቀን ውስጥ ለዐሥር ደቂቃ ብቻ ቃሉን በማንበብ ግማሽ ቀናቸውን ብርን በማሳደድ፣ የቀረውን ደግሞ የገዟቸውን ነገሮች በመንከባከብ ማሳለፋቸው ነው።
የጠፉትን እና የተጎዱትን እንዳንወድድ እንቅፋት የሆነብን ሐሳባችንን ሁሉ መንግሥተ ሰማይ ላይ ማድረጋችን ሳይሆን፣ በዚህ ዓለም ሐሳብ መጠመዳችን ነው፦ ምንም እንኳ በሐይማኖታዊ ሥርዓት ልንሸፋፍነው ብንሞክርም፣ እውነታው ይህ ነው።
ልቡ በከበረው የመንግስተ ሰማይ ተስፋ ከመያዙ የተነሣ በዚህ ዓለም ላይ ስደተኛ እና እንግዳ እንደሆነ የሚሰማው ሰው የት ይገኛል? የሚመጣውን ዓለም ውበት ቀምሶ የዚህን ዓለም አልማዞች እንደ ተራ ድንጋይ የሚያያቸው ሰውስ ይኖር ይሆን? ከዘላለም አንጻር ሲያያት ዓለም የጠበበችበት ያ ሰው ወዴት አለ?
በእርግጠኝነት ይህ ሰው በኢንተርኔት፣ በመብላት፣ በመጠጣት፣ በጭፈራ ወይም በመዝናናት የታሰረ አይደለም። ነገር ግን በእንግዳ ሃገር የሚኖር ነፃ ሰው ነው። በሕይወቱም የሚጠይቀው አንድ ጥያቄ ይህ ብቻ ነው፦ “በዚህ ዓለም ስደተኛ ሆኜ ሳለሁ በእግዚአብሔር ያለኝን ዘላለማዊ ደስታ እንዴት ነው መጨመር የምችለው?” ብሎ ይጠይቃል። መልሱም ደግሞ ሁልጊዜ አንድ ዓይነት ነው፦ የፍቅር ሥራዎችን በመሥራት የሚል ነው። ይህንንም የማደርገው በእግዚአብሔር የማገኘውን ደስታ በማስፋትና እና ምንም ዋጋ ቢያስከፍል በቻልኩት አቅም ሁሉ ለሌሎች ይህንን በማካፈል ነው ይላል።
ሃብታቸውን በሰማይ ያደረጉን ሰዎች ልብ ሊያስደስት የሚችለው አንድ ነገር ብቻ ነው፦ ያም የመንግስተ ሰማይን ሥራ መሥራት ነው። መንግስተ ሰማይ ደግሞ የፍቅር ዓለም ነው!
የፍቅርን እጆች የሚያስሯቸው የመንግስተ ሰማይ ገመዶች ሳይሆኑ የገንዘብ፣ የቅንጦት፣ የምቾት፣ የክብርና የራስ ወዳድነት ገመዶች ናቸው። እነዚህን ገመዶች የመበጠስ ኅይል ያለው ደግሞ ክርስቲያናዊው ተስፋ ነው። “ምክንያቱም በክርስቶስ ኢየሱስ ስላላችሁ እምነትና ለቅዱሳን ሁሉ ስላላችሁ ፍቅር ሰምተናል፤ ይህም የሆነው በሰማይ ተዘጋጅቶ ከተቀመጠላችሁ ተስፋ የተነሣ ነው” (ቈላስይስ 1፥4-5)።
በታላቅ እርግጠኝነት ደግሜ ልንገራችሁ፦ ፍቅር እንዳይኖረን የሚያደርገን ሰማይ-ተኮር መሆናችን ሳይሆን ምድር-ተኮርነታችን ነው። ታዲያ ክርስቲያን ለሆንን ሁሉ ነፃ ሊያወጣን የሚችለው ተስፋችን፣ ታላቁና ኀያሉ የፍቅር ወንዝ ነው።