ኢየሱስ በዚህ የልደት በዓል የሚፈልገው ምንድን ነው?

አባት ሆይ፤ እነዚህ የሰጠኸኝ፣ እኔ ባለሁበት እንዲሆኑ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝንም ክብሬን እንዲያዩ እፈልጋለሁ።

የዮሐንስ ወንጌል 17፥24 (አ.መ.ት.)

ኢየሱስ በዚህ ገና የሚፈልገው ምንድን ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ በጸሎቱ ውስጥ እናገኛለን። እግዚአብሔርን የሚለምነው ምንድን ነው? ዮሐንስ ወንጌል 17 የኢየሱስ ረጅሙ ጸሎቱ ነው። የመሻቱ ጥግ ደግሞ የተገለጸው ቁጥር 24 ላይ ነው።

በዓለም ሁሉ ካሉት ምሕረት የማይገባቸው ኀጢአተኞች ውስጥ እግዚአብሔር ለኢየሱስ “የሰጣቸው” አሉ። እነዚህ እግዚአብሔር ወደ ልጁ የሳባቸው ናቸው (ዮሐንስ 6፥44፣ 65)። ክርስቲያኖች ይባላሉ። ሞቶ የተነሣው አዳኝ እና ጌታ፣ ኢየሱስ መሆኑን በማመን የሕይወታቸው ሐብት አድርገው የተቀበሉት ናቸው (ዮሐንስ 1፥12፤ 3፥17፤ 6፥35፤ 10፥11፣ 17-18፤ 20፥28)። ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ እንደሚፈልግ ኢየሱስ ተናግሯል።

አንዳንድ ሰዎች እግዚብሔር ሰውን የፈጠረው ብቸኝነት ተሰምቶት ነው ሲሉ እንሰማለን። “እግዚአብሔር የፈጠረን አብረነው እንድንሆን ነው” ይላሉ። ኢየሱስ በዚህ ሐሳብ ይስማማ ይሆንን? በርግጥ ከእርሱ ጋር እንድንሆን በጣም እንደሚፈልግ ተናግሯል። ግን ለምን? ሙሉ ጥቅሱን ስናነበው ግልጽ ይሆናል። ኢየሱስ አብረነው እንድንሆን የሚፈልገው ለምንድን ነው?

“…ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ።”

በርግጥ ብቸኝነት ተሰምቶት ቢሆን ኖሮ፣ ስሜቱን የሚገልጸው በዚህ መንገድ አልነበረም፦ “ክብሬን ማየት እንዲችሉ ከእኔ ጋር እንዲሆኑ እፈልጋለሁ።” እንደውም ይህ የሚያስረዳው የእርሱን ብቸኝነት አይደለም። እርሱ ብቸኝነት ተሰምቶት ሳይሆን፣ የኛ ጉጉት ሲረካ ለማየት ካለው ፍላጎት የተነሣ ነው። ኢየሱስ ብቸኛ አይደለም። ከአባቱ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ልዩ በሆነ የሥላሴ ሕብረት በእጅጉ ረክቷል። ለሆነ ነገር የምንራበው እኛ እንጂ እርሱ አይደለም። ኢየሱስ በገና የሚፈልገው፣ እኛ የተፈጠርንለትን እርካታ እንድንቀምስ ነው። ለእኛ ያለው ፍላጎት እርሱን በማየት እና ክብሩን በማጣጣም ለዘለዓለም እንድንረካ ነው። ምናለ እግዚአብሔር ይህን እውነት በልባችን እንዲሰጥም ባደረገ! በርግጥ ኢየሱስ የፈጠረን ክብሩን እናይ ዘንድ ነው (ዮሐንስ 1፥3)።

ኢየሱስ ወደ መስቀል ሞት ከመሄዱ በፊት ከምንም ነገር የሚልቀውን ፍላጎቱን በአባቱ ፊት አቅርቧል። “እኔ ባለሁበት እንዲሆኑ … ክብሬን እንዲያዩ እፈልጋለሁ [እፈልጋለሁ!]”

ይህ ግን ኢየሱስ በዚህ የመጨረሻ እና ሁነኛ ጸሎት ከሚፈልገው ነገር ግማሹ ብቻ ነው። የተፈጠርነው ክብሩን እንድናይ እና እንድናጣጥም ነው ብዬ ነበር። በርግጥ ክብሩን ከማየት ባለፈ እንድናጣጥመው፣ እንድንወደው፣ እንድንደሰትበት፣ እና ልዩ ዋጋ እንድንሰጠው ነው የሚፈልገው? የመጨረሻውን ቁጥር፣ ቁጥር 26ን ተመልከቱ፦

“ለእኔ ያለህ ፍቅር በእነርሱ እንዲሆን፣ እኔም በእነርሱ እንድሆን፣ አንተን እንዲያውቁ አድርጌአለሁ፤ እንዲያውቁህም አደርጋለሁ።”

የጸሎቱ መጨረሻ ይሄ ነው። ኢየሱስ ለእኛ ያለው የመጨረሻው ግቡ ምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ፣ መልሱ የእርሱን ክብር ማየታችን ብቻ ሳይሆን አባቱ በሚወደው ዐይነት ፍቅር እኛ እርሱን እንድንወደው ነው። ልመናው፣ “ለእኔ ያለህ ፍቅር በእነርሱ እንዲሆን” የሚል ነው። የኢየሱስ ፍላጎት እና ዋና ግብ ክብሩን እንድናይ፣ ከዚያም በመቀጠል የምናየውን ኢየሱስን አባቱ በሚወደው ልክ እኛም እንድንወደው ነው። ይህንን ሲል ደግሞ እያለ ያለው አብ ለልጁ ያለውን ፍቅር እናስመስላለን አይደለም። አብ ለልጁ ያለውን ያንኑ ፍቅር እኛ ለልጁ ይኖረናል ማለት ነው። አብ ወልድን በሚወድበት በዚያው ፍቅር እኛ ወልድን እንወደዋለን። መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን የሚያፈስልን ጸጋ ይህ ነው፤ ከአብ የተሰጠን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የምናገኘው የኢየሱስ ፍቅር በሕይወታችን ይትረፈረፋል።

ኢየሱስ በገና ወቅት ከምንም ነገር በላይ የሚፈልገው፣ ምርጦቹ በአንድነት ተሰብስበው እነርሱ ከምንም ነገር በላይ የሚፈልጉትን ክብሩን ማየት እና ማጣጣም እንዲችሉ፣ እና አባቱ ልጁን በሚወድድበት መልኩ እንዲወድዱት ነው። የእኔም ጥልቅ መሻት በዚህ ገና ከእናንተ እና ከብዙ ሌሎች ሰዎች ጋር ሆኜ፣ ክርስቶስን በሙሉ ክብሩ ማየት እና ግማሽ ልብ በሆነው ሰዋዊ አቅማችን ልንገምት ከምንችለው በላይ በሆነ ፍቅር የምናየውን ኢየሱስን በሕብረት መውደድ እንችል ዘንድ ነው። በእነዚህ የገና ጥሞናዎች ማሳካት የምንፈልገው ግብ ይህ ነው። ኢየሱስን ልናየው እና ልናጣጥመው እንጓጓለን። የመጀመሪያ መምጣቱን በገና እያከበርን፣ ሁለተኛ መምጣቱን ደግሞ በናፍቆት እንጠባበቃለን።

ኢየሱስ በዚህ ገና ስለ እያንዳንዳችን የሚጸልየው ጸሎት ይህ ነው፦ “አባት ሆይ፣ ክብሬን አሳያቸው፣ ጨምረህም አንተ በእኔ ያለህን ደስታ ስጣቸው።” ክርስቶስን በእግዚአብሔር ዐይን ማየት ይሁንልን፤ በእግዚአብሔር ልብም ደግሞ መውደድ እና ማጣጣም ይሁንልን። የመንግሥተ ሰማይ ባሕርይው ይህ ነው። ኢየሱስ ለኀጢአተኞች ውድ ሕይወቱን ዋጋ በመክፈል ሊገዛ የመጣው ስጦታ ይህ ነው።