የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና። (ማቴዎስ 5፥5)
የዋህነት የሚጀምረው እምነታችንን በእግዚአብሔር ላይ በመጣል ነው። ከዚያ በመቀጠልም፣ እርሱን ስለምናምነው መንገዳችንን ወደ እርሱ እናቀናለን። ስጋቶቻችንን፣ ድካሞቻችንን፣ እቅዶቻችንን፣ ሥራችንን፣ ጤናችንን ሁሉ በእርሱ ላይ እንጥላለን።
ከዚያም ጌታችንን በትዕግስት እንጠብቀዋለን። ለራሱ ክብር እና ለእኛ ጥቅም ሲል ሁሉንም ነገር በጊዜው እንደሚሰራ በመተማመን፣ በጸጋው እና በኃይሉ በእምነት እንኖራለን።
እግዚአብሔርን ማመናችን፣ በትዕግስት መጠበቃችን፣ እንዲሁም ጭንቀቶቻችንን ሁሉ በእርሱ ላይ መጣላችን፣ ችኩል ለሆነ ንዴት እንዳንጋለጥ ይጠብቀናል። ከዚያ ይልቅ፣ ጉዳያችንን ለእግዚአብሔር አስረክበን፣ ቁጣውን ለእርሱ ትተን፣ ከፈለገ እንዲፈርድልን ሁሉን አሳልፈን እንሰጠዋለን።
እናም፣ ያዕቆብ እንዳለው፣ በዚህ ስንታመን ለመስማት የፈጠንን፣ ለመናገር የዘገየን እንሆናለን (ያዕቆብ 1፥19)። ደግሞም ምክንያታዊ እና ለመታረም ዝግጁ በመሆን እናድጋለን (ያዕቆብ 3፥17)። ያዕቆብ ይህንን “ከጥበብ የሆነ መልካም አኗኗር” ሲል ይጠራዋል (ያዕቆብ 3፥13)።
የዋህነት መማርን ይወድዳል። የወዳጁንም ግሳፄ እንደመልካም ይቀበላል (ምሳሌ 27፥6)። በኀጢአት የሚመላለስን ሰው አግኝቶ መገሰፅ ሲያስፈልገውም፣ የራሱን ውድቀት ሳይክድ በእግዚአብሔር ፀጋ ላይ ሙሉ ሙሉ ጥገኛ መሆኑን ከልቡ በማመን ይመክራል (ገላትያ 6፥1)።
በየዋህነት ውስጥ ያሉት ዝምተኝነት፣ ግልጽነትና ራስን ክፍት ማድረግ እጅግ ያማሩ ቢሆኑም ዋጋ ግን ያስከፍላሉ። በኀጢአታዊው ተፈጥሮአችን ከሆንነው ጋር ፈፅሞ ተቃራኒ ናቸው። መለኮታዊ እርዳታን ይሻሉ።
የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ከሆናችሁ፣ እርሱን አምናችሁ መንገዳችሁን ወደርሱ ካቀናችሁ፣ እንዲሁም በትዕግስት ከጠበቃችሁት፣ እግዚአብሔር እናንተን መርዳት ጀምሯል ማለት ነው። ይህንንም እርዳታውን ሳያቋርጥ ይቀጥላል።
እናንተን የሚረዳበት ቀዳሚው መንገድም፣ ከኢየሱስ ጋር ወራሽ እንደሆናችሁ፣ ዓለምና ሞላዋ ሁሉ በክርስቶስ በኩል የእናንተ እንደሆነ በማስታወስ እና ልባችሁን በማፅናት ነው (1ኛ ቆሮንቶስ 3፥21-23)። አስታውሱ፣ የዋሆች ምድርን ይወርሳሉ።