ልክ የሆነ ኀፍረት ምንድን ነው? | ሚያዚያ 11

የኀጢአት ባሮች ሳላችሁ ከጽድቅ ነጻ ነበራችሁ። አሁን ከምታፍሩበት ነገር ያን ጊዜ ምን ጥቅም አገኛችሁ? የዚያ ነገር ውጤት ሞት ነው። (ሮሜ 6፥20–21)

አንድ ክርስቲያን፣ እግዚአብሔርን ያዋርዱ የነበሩትን የቀደሙ የክፋት ምግባሮቹን ዓይኖቹ ተከፍተው ሲያያቸው በሚገባ ያፍራል። ጳውሎስ ለሮም ቤተ ክርስቲያን “የኃጢአት ባሪያዎች ሳላችሁ . . . አሁን ከምታፍሩበት ነገር ያን ጊዜ ምን ጥቅም አገኛችሁ?” ብሎ ይጠይቃቸዋል።

በአንድ ወቅት እግዚአብሔርን በሚያዋርድ መንገድ የኖርነውን ሕይወት በሕመም ስሜት ወደ ኋላ መመልከት ትክክል የሚሆንበት ጊዜ አለ። በእርግጥ፣ ይህን ጉዳይ በማሰብ ሽባ መሆን የለብንም። ነገር ግን ልቡ ስስ የሆነ የትኛውም ክርስቲያን፣ ምንም እንኳ ሁሉንም ነገር ከጌታው ጋር በይቅርታ አወራርዶ የጨረሰ ቢሆንም፣ የልጅነት ሞኝነቱን ወደ ኋላ መለስ ብሎ ሲያስብ የኀፍረት ስሜት ላይሰማው አይችልም።  

ተገቢ የሆነ ኀፍረት በጣም ጤናማ እና እንዲያውም የሚቤዥ / የሚያድን ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች፦ “በዚህ መልእክት ላይ ላለው ቃላችን የማይታዘዝ ማንም ቢኖር፣ እንደዚህ ያለውን ሰው በጥንቃቄ ተከታተሉት፤ በሥራውም እንዲያፍር ከእርሱ ጋር አትተባበሩ” ብሏቸዋል (2ኛ ተሰሎንቄ 3፥14)። ይህ ማለት ኀፍረት ጌታን አግኝቶ በመለወጥ (Conversion) ውስጥ ትክክለኛ የድነት እርምጃ ነው ማለት ነው። ደግሞም በአማኞች ሕይወት ውስጥ አንዳንዴ ከሚያጋጥም መንፈሳዊ ድንዛዜ እና ኃጢአት በንስሓ ለመመለስ ትክክለኛው መንገድ ነው። ተገቢ የሆነ ኀፍረት እንደ ምንም ብለን ልናመልጠው የሚገባ ነገር አይደለም። እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖረው የሚያስችል ጠቃሚ ነገር ነው።

ስለዚህ፤ አንድን ኀፍረት እግዚአብሔርን ማዕከላዊ ያደረገ መሆኑን ወይም አለመሆኑን በማጤን፣ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ተንተርሰን መድረስ እንችላለን።            

ያላግባብ ለሆነ ኀፍረት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመዘኛው እግዚአብሔር-ተኮር መሆኑ ነው። አንድ ድርጊት፣ በሌሎች ሰዎች ፊት ምንም ያህል ደካማ፣ ሞኝ ወይም የተሳሳትን ቢያስመስለንም፣ እግዚአብሔርን የሚያከብር ነገር ከሆነ ግን ኀፍረት ሊሰማን አይገባም። ወይም፣ በሌላ አገላለጽ፣ አንድ አሳፋሪ ሁኔታ ወስጥ በሆነ መንገድ በክፋት እስካልተሳተፍን ድረስ ኀፍረት ቢሰማን፣ ይህ አግባብነት የሌለው ኀፍረት ነው።

ተገቢ ለሆነው ኀፍረት ደግሞ የሚቀርበው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመዘኛ ይህ ነው፦ አንድ ድርጊት በሌሎች ሰዎች ዓይን ፊት የቱንም ያህል ጠንካራ፣ ጥበበኛ ወይም ትክክል አስመስሎን፣ ነገር ግን፣ ያ ነገር እግዚአብሔርን የሚያሳፍር ወይም የሚያዋርድ ከሆነ፣ እጃችን ስላለበት ብቻ ኀፍረት ሊሰማን ይገባል።

ኀፍረት ሊሰማን የሚገባው እግዚአብሔርን በሚያዋርዱ አስተሳሰቦች እና ድርጊቶች ነው። አስተሳሰቦቹ እና ድርጊቶቹ እግዚአብሔርን የሚያከብሩ ከሆኑ ደግሞ፣ ምንም ያህል ዓለም ሊያሳፍረን ቢጥርም፣ በፍጹም ኀፍረት ሊሰማን አይገባም።