ዓላማችሁ ምንድር ነው? | ታሕሳስ 2

እንግዲህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ፣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ፣ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት። … በእርሱ በኩል ለእግዚአብሔር አብ ምስጋና እያቀረባችሁ፣ በቃልም ሆነ በተግባር የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት። (1ኛ ቆሮንቶስ 10፥31ቈላስይስ 3፥17)

ጠዋት ከእንቅልፍ ተነሥታችሁ ቀኑን ስትጋፈጡ፣ ስለዚያ ቀን ምን ተስፋ ታደርጋላችሁ? የቀኑ መጀመሪያ ላይ ሆናችሁ፣ ወደ ቀኑ መጨረሻ ስትመለከቱ፣ በሕይወት ስለዋላችሁ ምን እንዲሆን ወይም ምን እንዲፈጠር ትፈልጋላችሁ?

“እንዲህ ብዬ እንኳ አላስብም። በቃ እነሣለሁ፣ ከዚያም ማድረግ ያለብኝን ነገር አደርጋለሁ” የሚል ከሆነ መልሳችሁ፣ ራሳችሁን መሰረታዊ ከሆነው የጸጋ፣ የምሪት፣ የጥንካሬ፣ እንዲሁም የፍሬያማነት እና የደስታ ምንጭ ትቆርጣላችሁ። በእነዚህ ጥቅሶች እና በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ እግዚአብሔር ቀናቶቻችንን በማስተዋል፣ አንድ ጉልህ ነገርን ዓላማ ማደረጋችንን እንደሚፈልግ ግልጽ ነው።

የእግዚአብሔር የተገለጠ ፈቃድ፣ በማለዳ በምትነሱበት ጊዜ፣ ቀኑን ሙሉ የምታደርጉትን ነገር፣ ሁኔታዎች ብቻ እንዲወስኑላችሁ በመፍቀድ በከንቱ እንድትንሳፈፉ ሳይሆን፣ አንድ ነገርን በማቀድ፣ ግልጽ የሆነ ዓላማ ላይ ትኩረት እንድታደርጉ ነው። እዚህ ጋር እየተናገርኩ ያለሁት ለልጆች፣ ለጎረምሶች፣ ለጎልማሶች፣ ላላገቡ፣ ደግሞም ለባለ ትዳሮች፣ ለመበለቶች፣ ለእናቶች፣ እንዲሁን በየትኛውም ዓይነት የንግድ እና ሙያ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ሁሉ ነው።

ዓላማ ቢስነት ሕይወት አልባነት ነው። በጓሯችን ውስጥ ያሉ የሞቱ ቅጠሎች ከምንም ነገር በላይ ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ – ከውሻም፣ ከልጆችም፣ ከምንም ነገር የበለጠ። ነፋስ በዚህ መንገድ የነፈሰ እንደሆነ፣ በዚህ መንገድ አብረው ይነፍሳሉ። ነፋስ በዚያ መንገድ የሄደ እንደሆነ፣ እነርሱም በዚያ መንገድ ይሄዳሉ። ይወድቃሉ፤ ይገለባበጣሉ፤ ይዘላሉ፤ አጥር ላይ ይለጠፋሉ፤ ነገር ግን ምንም ዓላማ የላቸውም። በእንቅስቃሴ የተሞሉ ቢሆኑም፣ ሕይወት ግን የላቸውም።

እግዚአብሔር በአምሳሉ ሰዎችን የፈጠራቸው፣ በጓሮ ውስጥ እንደሚነፍሱ ሕይወት እንደሌላቸው ቅጠሎች ዓላማ ቢስ እንዲሆኑ አይደለም። የፈጠረን በዓላማ እንድንኖር ነው። በቀኖቻችን ሁሉ ትኩረት እና ግብ እንዲኖረን ነው። የዛሬ ትኩረታችሁ ምን ይሆን? የአዲስ ዓመት ግባችሁስ? ለመጀመር ጥሩ የሆነው ቦታ ይህ ጥቅስ ነው፦ “እንግዲህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ፣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ፣ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” (1ኛ ቆሮንቶስ 10፥31)።