እግዚአብሔርን መውደድ ማለት ምን ማለት ነው? | ግንቦት 10

እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤ አንተን ከልብ እሻለሁ፤ ውሃ በሌለበት፣ በደረቅና በተራቈተ ምድር፣ ነፍሴ አንተን ተጠማች፤ ሥጋዬም አንተን ናፈቀች። ስለዚህ በመቅደስ ውስጥ አየሁህ፤ ኀይልህንና ክብርህንም ተመለከትሁ። (መዝሙር 63፥1-2)

እንደ ዳዊት ያለውን ልብ ሊያረካ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ዳዊት እንደ እግዚአብሔር ልብ የሆነ ሰው ነበር። የተፈጠርነው እንዲያ እንድንሆን ነበር።

እግዚአብሔርን መውደድ ማለት በዋነኛነት በእርሱ መርካት ማለት ነው። በስጦታዎቹ ብቻ ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር በራሱ — ማለትም በከበረው ማንነቱ — መርካት ማለት ነው።

እግዚአብሔርን መውደድ ትዕዛዛቱን ሁሉ መታዘዝን ያካትታል። እንዲሁም ቃሉን ሁሉ ማመንን እና ስለ ስጦታዎቹ ሁሉ እርሱን ማመስገንን ይጨምራል። ነገር ግን ይህ ሁሉ ተጨማሪ ነው። እግዚአብሔርን የመውደድ ዋነኛው ትርጉም፣ እርሱን ማድነቅ እና በእርሱ ደስ መሰኘት ነው። ይህም ደስታ ነው የምናደርገውን ነገር ሁሉ በእውነት ለእርሱ ክብር እንዲውል የሚያደርገው።

ይህ ደግሞ እውነት እንደሆነ ከእግዚአብሔር ቃል፣ እንዲሁም የምናየውን ነገር በማስተዋል መረዳት እንችላለን። እንደተከበርን የሚሰማን እና ደስ የምንሰኘው ተገድደው በሚያገለግሉን ሰዎች ነው ወይስ መገኘታችን እያስደሰታቸው በሚያገለግሉን ሰዎች?

ባለቤቴ፣ “ካንቺ ጋር ጊዜዬን ሳሳልፍ ደስ ይለኛል” ስላት ክብር ይሰማታል። የእኔ መደሰት የእርሷን ውበት እና ልህቀት ያስተጋባል። ከእግዚአብሔርም ጋር እንዲሁ ነው። እርሱ በእኛ በሙላት የሚከብረው፣ እኛ በእርሱ በሙላት ደስ ስንሰኝ ነው።

ማናችንም በእግዚአብሔር ፍፁም እርካታን ማግኘት ላይ አልደረስንም። አንዳንድ ምድራዊ ምቾቶቼን ሳጣ በልቤ ያለውን ማጉረምረም አደምጥና በራሴ በእጅጉ አዝናለሁ። ነገር ግን እግዚአብሔር መልካም እንደሆነ ቀምሻለሁ። በእግዚአብሔር ጸጋ፣ የዘላለም ደስታ ምንጭ እርሱ እንደሆነ አሁን ተረድቻለሁ።

እናም፣ ሰዎችን ሁሉ ወደዚህ ደስታ በመጎተት ቀኖቼን ሁሉ ባሳልፍ ደስ ይለኛል። ከዘማሪውም ጋር አብረን እንዲህ እንበል፦ “እግዚአብሔርን አንዲት ነገር እለምነዋለሁ፤ እርሷንም እሻለሁ፤ ይኸውም በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ውበት አይ ዘንድ፣ በመቅደሱም ሆኜ አሰላስል ዘንድ ነው” (መዝሙር 27፥4)።