ገንዘብን መውደድ ምን ማለት ነው? | ሐምሌ 25

የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው ” (1ኛ ጢሞቴዎስ 6፥10)።

ጳውሎስ ይህን ሲጽፍ ምን ማለት ፈልጎ ነበር? ኃጢአት በምንሰራበት ጊዜ ሁሉ አዕምሯችን ስለ ገንዘብ ያስባል ማለቱ አይደለም። ምክንያቱም ስለ ገንዘብ ሳናስብ ብዙ ኃጢአት እንሠራለን።

የእኔ ምልከታ ይህ ነው፦ በዓለም ላይ ያሉ ክፋቶች ሁሉ ገንዘብን ከሚወድ ልብ የሚመነጩ ናቸው ማለቱ ነው።

ታዲያ ገንዘብን መውደድ ማለት ምን ማለት ነው? የወረቀቱን ቀለም ወይም የሳንቲሞቹን ቅርጽ ማድነቅ ማለት አይደለም። ገንዘብን መውደድ ምን ማለት እንደሆነ ለማወቅ ገንዘብ ራሱ ምንድን ነው ብላችሁ ልትጠይቁ ይገባል። መልሱም፣ ገንዘብ በቀላሉ የሰውን ሀብት ለማመልከት የሚያገለግል ምልክት ነው። ገንዘብ ማለት ከእግዚአብሔር ይልቅ ከሌሎች ሰዎች ልታገኝ የምትችለውን የትኛውንም ነገር ይወክላል።

እግዚአብሔር ግን የሚገበያየው በጸጋ እንጂ በገንዘብ አይደለም፦ “እናንት የተጠማችሁ ሁሉ ኑ፣ እናንት ገንዘብ የሌላችሁ፣ ወደ ውሆች ኑ፤ ኑና ግዙ፤ ብሉም“ (ኢሳይያስ 55፥1)። ገንዘብ የሰው ሀብት መገበያያ ምንዛሬ ነው። ስለዚህ ገንዘብን የሚወድ ልብ ማለት የሰው ኃይል ሊያቀርበው በሚችለው ነገር ላይ ተስፋውንና እምነቱን የሚጥል ልብ ነው። ደስታውንም የሚቀዳው ከዚያ የምድራዊ ሀብት ወንዝ ነው።

ስለዚህ፣ ገንዘብ መውደድ በገንዘብ ከመታመን ጋር ወይም እምነታችንን ገንዘብ ላይ ከመጣል ጋር ተመሳሳይ ነው። ገንዘብ ፍላጎታችንን ሁሉ እንደሚያሟላ እና ደስተኛ እንደሚያደርገን ማመንና እርግጠኛ መሆን ነው።

ገንዘብን መውደድ በእግዚአብሔር የወደፊት ጸጋ መታመን ጋር ይጋጫል። ነገ በገንዘብ ሊያገኙት ወይም ሊያስጠብቁት በሚችሉት ምድራዊ ሀብት ላይ ያለ እምነት ነው። ስለዚህ ገንዘብን መውደድ ወይም በገንዘብ መታመን በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ያለማመን ሌላኛው ገጽታ ነው። ኢየሱስ በማቴዎስ 6፥24 ላይ “አንድ ሰው ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም፤ እግዚአብሔርን እና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም” ብሏል።

በተመሳሳይ ጊዜ በእግዚአብሔር እና በገንዘብ መታመን አይቻልም። በአንዱ ማመን በሌላው አለማመን ነው። ገንዘብን የሚወድ ልብ ደስታውን የሚያገኘው በዚያ ነው። ደስታውን እና ተስፋውን ደግሞ በገንዘብ የሚያኖር ነፍስ፣ እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ለእርሱ የሆነለትን ሁሉ የዘነጋ እና በእግዚአብሔር የማይረካ ነፍስ ነው።