“ጠላቶቻችሁን ውደዱ ፤ ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ።” (ማቴዎስ 5፥44)
ለጠላቶቻችሁ መጸለይ ጥልቅ ከሆኑ የፍቅር ዓይነቶች አንዱ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት ደግሞ ለጠላቶቻችሁ መጸለይ ማለት ጥሩ ነገር እንዲሆንላቸው በእውነት መፈለግ ማለት ስለሆነ ነው።
ለጠላቶቻችሁ መልካም እንዲሆንላቸው ከልብ ሳትመኙ፣ ጥሩ ነገሮችን ግን ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ። ነገር ግን ለእነርሱ ስትጸልዩ ልባችሁን በሚያውቀው በእግዚአብሔር ፊት ነው። ደግሞም ጸሎት ማለት ስለ እነርሱ ወደ እግዚአብሔር መማለድ ነው።
የጸሎቱ ይዘት ምንም ሊሆን ይችላል። እንዲለወጡ ሊሆን ይችላል። በንስሓ እንዲመለሱም ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ደግሞ በልባቸው ውስጥ ባለው ክፋት ላይ እንዲነቁበት ሊሆን ይችላል። አልያም በሽታንም ሆነ የሆነ መከራን ተጠቅሞም ቢሆን፣ እግዚአብሔር ከኃጢአታቸው አዘቅት ውስጥ እንዲያወጣቸው ሊሆን ይችላል። ብቻ ግን ኢየሱስ እዚህ ጋር እያለው ያለው ጸሎት ሁልጊዜም ለጥቅማቸው የሚጸለይ ነው።
ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተንጠልጥሎ ያደረገው ይህንን ነው፦
አባት ሆይ፤ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው።
(ሉቃስ 23፥34)
እስጢፋኖስም በድንጋይ ሲወገር ያለው እንዲህ ነው፦
ተንበርክኮ በታላቅ ድምፅ፣ “ጌታ ሆይ፤ ይህን ኀጢአት አትቍጠርባቸው!” ብሎ ጮኸ።
(የሐዋርያት ሥራ 7፥60)
ኢየሱስ እየጠራን ያለው ጠላቶቻችንን መንገድ ላይ ሰላም እንድንላቸውና የሚያስፈልጋቸው ነገር ሲኖር እንድንረዳቸው ብቻ አይደለም (ማቴዎስ 5፥47)። ከጎናችን በሌሉበት ጊዜም እንኳ፣ ለእነርሱ መልካሙን ሁሉ እንድንመኝና ይህንን ምኞታችንንም በጸሎት እንድንገልጽ እየጠራንም ጭምር ነው።
ልባችን መዳናቸውን ሊመኝ፣ ከእኛም ጋር በሰማይ መገኘታቸውንና ዘላለማዊ ደስታቸውንም ሊሻ ይገባዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ሕይወትን ከባድ ላደረጉበት ለአይሁድ ሕዝብ እንደጸለየ እኛም የምንጸልይበትን ጸጋ እግዚአብሔር ይስጠን።
“የልቤ ምኞት፣ እግዚአብሔርንም የምለምነው እንዲድኑ ነው።”
(ሮሜ 10፥1)