ሰው አንድ ጊዜ ሊሞት ከዚያም በኋላ በፍርድ ፊት ሊቆም ተወስኖበታል። ክርስቶስ የብዙ ሰዎችን ኀጢአት ለመሸከም፣ እንዲሁ አንድ ጊዜ መሥዋዕት ሆኖአል፤ ሁለተኛ ጊዜም ይገለጣል፤ ይህም ለሚጠባበቁት ድነትን ለማምጣት እንጂ ኀጢአትን ለመሸከም አይደለም። (ዕብራውያን 9፡27-28)
የኢየሱስ ሞት ብዙ ኃጢአትን ይሸከማል። ይህ የክርስትና ደግሞም የወንጌል እና ታላቅ የሆነው የእግዚአብሔር የማዳን ስራ ልብ ነው። ክርስቶስ ሲሞት ኃጢአትን ተሸክሞ ነበር። የራሱ ያልሆነን ኃጢአት ወሰደ። ከኃጢአት ነጻ ይሆኑ ዘንድ ሌሎች በሰሩት ኃጢአት እርሱ መከራን ተቀበለ።
እንደ ዋና ችግር አያችሁትም አላያችሁትም፣ ይህ በሕይወታችሁ ውስጥ ላለው ለታላቁ ችግር መልስ ነው። ኃጢአተኞች ብንሆንም ከእግዚአብሔር ጋር እንዴት መታረቅ እንደምንችል መልስ አለ። መልሱም ይህ ነው፦ የክርስቶስ ሞት “የብዙ ሰዎችን ኀጢአት ለመሸከም” የቀረበ መሥዋዕት ነው። ኃጢአታችንን አንሥቶ እስከ መስቀል በመሸከም፣ በዚያ ልንሞት የሚገባንን ሞት እርሱ ሞተ።
ታዲያ ይህ ስለ እኔ ሞት ምን እያለ ነው? “አንድ ጊዜ ሊሞት ተወስኖበታል [እኔንም ጭምር]።” የእኔ ሞት ከአሁን በኋላ ለቅጣት አይደለም ማለት ነው። የእኔ ሞት የኃጢአት ቅጣት አይደለም። ኃጢአቴ ከእኔ ተወስዷል። ኃጢአቴ በክርስቶስ ሞት “ተወግዷል”። ክርስቶስ ቅጣቱን ወስዶታል። ታዲያ ለምንድነው የምሞተው? ምክንያቱም እግዚአብሔር ሞትን በአሁኑ ዓለም ላይ፣ በገዛ ልጆቹም መካከል እንኳ፣ ለኃጢያት አስፈሪነት የማይለወጥ ምስክር ሆኖ እንዲኖር አድርጓል። በሞታችን አሁንም በዓለም ውስጥ ያሉትን የኃጢአትን ውጫዊ ውጤቶችን እናሳያለን። ነገር ግን ለእግዚአብሔር ልጆች ሞት ከእንግዲህ ወዲያ በእነርሱ ላይ ያለው ቁጣው አይደለም። ኩነኔ ሳይሆን ወደ ድነት መግቢያ በር ሆኗል።