“ነገር ግን እኔ ወደዚህ፣ ትሑት ወደ ሆነና መንፈሱ ወደ ተሰበረ፣ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ።” (ኢሳይያስ 66፥2)
ቀና የሆነ ልብ የመጀመሪያው ምልክቱ በእግዚአብሔር ቃል መንቀጥቀጡ ነው።
ኢሳይያስ 66፣ እግዚአብሔርን በሚያስደስተው መንገድ በሚያመልኩት ሰዎች እና በማያስደስተው መንገድ በሚያመልኩት ሰዎች መካከል ያለውን ችግር ይመለከታል። ቁጥር 3 መሥዋዕታቸውን ስለሚያቀርቡ ጠማማ ሰዎች ሲናገር፣ “ነገር ግን ወይፈን የሚሠዋልኝ ሰው እንደሚገድል ነው” ይላል። መሥዋዕታቸው ከነፍስ ግድያ እኩል በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነበር። ግን ለምን?
በቁጥር 4 ላይ እግዚአብሔር፣ “በተጣራሁ ጊዜ የመለሰ፣ በተናገርሁ ጊዜ ያደመጠ ሰው የለምና” በማለት ያስረዳል። የሕዝቡ መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ የነበረው የእርሱን ድምፅ ስላልሰሙ ነበር። ታዲያ ግን ለምን እግዚአብሔር የሌሎቹን ሰዎች ጸሎት ሰማ? በቁጥር 2 ላይ እግዚአብሔር፣ “ነገር ግን እኔ ወደዚህ፣ ትሑት ወደ ሆነና መንፈሱ ወደ ተሰበረ፣ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ” ይላል።
ከዚህ በመነሳት፣ እግዚአብሔር በጸሎታቸው የሚደሰትባቸው ቅን ሰዎች እነማን ናቸው ከተባለ፣ በእግዚአብሔር ቃል የሚንቀጠቀጡ ናቸው ብለን መደምደም እንችላለን። ጌታ የሚመለከተው እንዲህ ያሉትን ሰዎች ነው።
ስለዚህ፣ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝበት የቅኖች ጸሎት የሚመጣው በእግዚአብሔር መገኘት ፊት ሲሆን ከሚጠነቀቅ ልብ ነው። እንዲህ ያለ ልብ በውድቀቱ ስለሚጸጸት፣ ከእግዚአብሔር አሳብ እጅግ መራቁን ስለሚያውቅና ሊፈረድበት የሚገባ አቅመ ቢስ እንደሆነ ስለሚሰማው፣ የእግዚአብሔርን ቃል ሲሰማ ይንቀጠቀጣል።
ዳዊት በመዝሙር 51፥17 ላይ ያለው ይህንኑ ነው፦ “እግዚአብሔር የሚቀበለው መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም” ይላል። ጸሎታችን በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የሚኖረው፣ በተሰበረና በተዋረደ ልብ በፊቱ ስንቀርብ ነው። የትሁታን ልብ በእግዚአብሔር ቃል ፊት ዘወትር ይንቀጠቀጣል።