አሁን ግን ከዚህ የሚበልጠውን ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ አላፈረም፤ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና። (ዕብራውያን 11፥16)
እግዚአብሔር ስለ አብርሃም፣ ስለ ይስሐቅና ስለ ያዕቆብ የተናገረውን፣ ስለ እኔም ቢናገር ብዬ እጅግ እመኛለሁ፦ “አምላክህ ተብዬ ልጠራ አላፍርም።”
ይህንን ስንል ታላቅ ጥንቃቄ ቢያስፈልገውም፣ እግዚአብሔር አምላካችን ተብሎ በመጠራቱ “ይኮራል” ማለታችን አይደለምን? ታዲያ ይህንን አስደናቂ ዕድል፣ በዕብራውያን 11፥16 ላይ በሁለት ምክንያቶች ተከብቦ እናገኘዋለን — አንድ ከፊት፣ አንድ ደግሞ ከኋላ።
በመጀመሪያ፣ ከፊት ያለውን እንመልከት፦ “እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ አላፈረም፤ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና።”
አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ ያላፈረበትን የመጀመሪያውን ምክንያት ሲሰጥ፣ ለእነርሱ የሆነ ነገርን ስላደረገላቸው ነው ይለናል። ከተማን አዘጋጀላቸው — ሰማያዊት የሆነችን፣ “እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ” (ዕብራውያን 11፥10)። ስለዚህ፣ አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ ያላፈረበት የመጀመሪያው ምክንያት እርሱ ለእነርሱ ስለሠራላቸው ነው፤ እንጂ በተቃራኒው አይደለም።
አሁን ደግሞ ከኋላ የሰጠውን ምክንያት እንመልከት። እንዲህ ይላል፦ “ከዚህ የሚበልጠውን ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ አላፈረም።”
“ስለዚህ” የሚለው ቃል፣ እግዚአብሔር ለምን አምላካችን ተብሎ ለመጠራት እንዳላፈረ ምክንያት እየሰጠ እንደሆነ ያመለክታል። ምክንያቱ ናፍቆታቸው ነው። የሚበልጥን አገር ይናፍቃሉ — ይህችም ከሚኖሩባት ምድራዊ አገር እጅግ የተሻለች ናት። እግዚአብሔር ያለባት ሰማያዊ አገር ናት።
ይህችን የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነች ሰማያዊ ከተማ ዓለም ልትሰጥ ከምትችለው ነገር ሁሉ በላይ ስንናፍቅ፣ እግዚአብሔር አምላካችን ተብሎ ሊጠራ አያፍርም። እርሱ ለእኛ ሊሆንልን የገባውን ቃል ሁሉ አብዝተን ስናምን፣ እርሱ አምላካችን በመሆኑ ይኮራል። ይህ ደግሞ መልካም ዜና ነው።
ስለዚህ፣ እግዚአብሔር ወዳዘጋጀልን ቅድስቲት ከተማ፣ ወደ ተሻለችው አገር፣ ዓይኖቻችሁን አንሱ። በፍጹም ልባችሁም ናፍቋት። እግዚአብሔርም አምላካችሁ ተብሎ ሊጠራ አያፍርም።