በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሤት አድርጎ እንዲህ አለ፤ “የሰማይና የምድር ጌታ፤ አባት ሆይ፤ ይህን ሁሉ ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን፣ አባት ሆይ፤ ይህ የአንተ በጎ ፈቃድ ሆኗልና።” (ሉቃስ 10፥21)
በወንጌላት መጻሕፍት፣ “ኢየሱስ ሐሤት አደረገ” ተብሎ ከተጻፈባቸው ሁለት ቦታዎች ውስጥ፣ ይህ አንደኛው ነው። ይህ ክፍል፣ 70ዎቹ ደቀ-መዛሙርት ከስብከት ጉዟቸው ተመልሰው፣ ስኬታቸውን ለኢየሱስ የተናገሩበት ክፍል ነው።
እዚህ ጋር ሦስቱም የሥላሴ አካላት እየተደሰቱ እንደሆነ አስተውሉ፦ ኢየሱስ ሐሴት እያደረገ ነው፤ ነገር ግን ሐሴት የሚያደርገው በመንፈስ ቅዱስ ነው። ይህን ክፍል፣ መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስን በደስታ እየሞላውና ለደስታ እየገፋፋው ነው ብለን ልንረዳው እንችላለን። ከዚያም፣ መጨረሻ ላይ የእግዚአብሔር አብን ደስታ ይገልጽልናል። “አዎን፣ አባት ሆይ፤ ይህ የአንተ በጎ ፈቃድ ሆኗልና።” — ማለትም አንተ ይህን በማድረግ ተደስተሃል።
ታዲያ፣ በዚህ ቦታ ላይ ሦስቱንም የሥላሴ አካላት እያስደሰታቸው ያለው ነገር ምንድን ነው? የዚህ መልስ፦ ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ይልቅ ለሕፃናት እውነትን መግለጥ የእግዚአብሔር ነፃ የፍቅር ምርጫ መሆኑ ነው። “የሰማይና የምድር ጌታ፤ አባት ሆይ፤ ይህን ሁሉ ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ።”
ታዲያ እግዚአብሔር አብ ከአንዳንዶች ደብቆ ለሌሎች የሚገልጠው ምስጢር ምንድን ነው? ሉቃስ 10፥22 የዚህን መልስ ይሰጠናል፦ “ወልድ ማን እንደ ሆነ ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም።” ስለዚህ፣ አብ የሚገልጠው እውነተኛ የሆነውን የልጁን መንፈሳዊ ማንነት ነው ማለት ነው።
70ዎቹ ደቀ-መዛሙርት ከወንጌል ተልዕኳቸው ተመልሰው ውጤታቸውን በሚናገሩበት ሰዓት፣ ኢየሱስ እና መንፈስ ቅዱስ፣ በእግዚአብሔር አብ በጎ ፈቃድ ደስ እንደተሰኙ እናያለን — ይኸውም፣ ልጁን ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውሮ ለሕፃናት ለመግለጥ በደስታ በመፍቀዱ ነው።
የዚህ ክፍል ዋና ሐሳብ፣ በእግዚአብሔር ተመራጭ የሆኑ የሆኑ ዓይነት ሰዎች መኖራቸውን ማሳየት አይደለም። ነገር ግን፣ እግዚአብሔር ለመመረጥ ከማንም በላይ ብቁ ያልሆኑና መመረጥ የማይገባቸውን ሰዎችን በራሱ ነፃ ፈቃድ ለፀጋው መምረጡን መግለጥ ነው።
ሰዎች ሽልማትን በሚያዩበት መንገድ እግዚአብሔር አይስማማም። ለሰዎች፣ ሽልማት የመልካም ሥራ ውጤት ነው። በራሳቸው ከሚታመኑ ጥበበኞች ራሱን ደብቆ፣ ረዳት ለሌላቸው እና ብቁ ላልሆኑ ምስኪኖች ይገልጣል።
ከነጻ ፀጋ ውጪ ተስፋ የሌላቸውን ምስኪኖች አብ ሲያበራላቸውና ሲያድናቸው ሲያይ፣ ኢየሱስ በአባቱ ምርጫ በመንፈስ ቅዱስ ሐሤት ያደርጋል።
እኛም ይህንን ስንረዳና በእርግጥ የተመረጥን ልጆቹ መሆናችንን ስናውቅ፣ እኛም ከእርሱ ጋር የዚህ ደስታው ተካፋይ እንሆናለን።