“ሥጋዊ ምኞቱን ለማርካት የሚዘራ፣ ከሥጋ ጥፋትን ያጭዳል፤ መንፈስን ለማስደሰት የሚዘራ ግን ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል።” (ገላትያ 6፥8)
እምነት በተቻለ መጠን የእግዚአብሔርን ጸጋ ለመለማመድ የማይጠገብ ፍላጎት አለው። ይህንንም ለማግኘት፣ የእግዚአብሔር ጸጋ በነፃነት ወደ ሚፈስበት የፍቅር ወንዝ ራሱን ያስጠጋል።
እስቲ አስቡት። ፍቅር የሚጠይቀውን ዋጋ ለመክፈል፣ የሌሎችን ሸክም ለመሸከምና ከተመቻቸ ኑሮአችን በፈቃደኝነት ለመውጣት የሚያስችል ሌላ ምን ኅይል አለ?
- ዓይን አፋሮች ሆነን እንግዳን ሰላም ለማለት?
- የበደሉን ይቅር ለማለትና እርቅን ለመለመን?
- ለመጀመሪያ ጊዜ ዐሥራትን ለመክፈል?
- ጭምቶች እንኳ ሆነን ሳለ ለጓደኞቻችን ስለ ክርስቶስ ለመናገር?
- የሥራ ባልደረቦቻችንን ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመጋበዝ?
- ድንበር አቋርጠን ወንጌሉን ለመናገር?
- ለሱሰኞች የበጎ አድራጎት አገልግሎት ለመጀመር?
- የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማገልገል?
- በማለዳ ጸሎት ራሳችንን ለማትጋት?
- እነዚህን ሁሉ እንድናደርግ የሚገፋፋን ምንድን ነው?
ከእነዚህ ዋጋ ከሚያስከፍሉ የፍቅር ድርጊቶች ውስጥ አንዳቸውም እንዲሁ አይመጡም። በአዲስ ፍላጎት ተገፋፍተዋል፤ ይኸውም የእግዚአብሔርን ጸጋ በሙላት ለመለማመድ በሚሻ የእምነት ፍላጎት ነው። እግዚአብሔርን እንፈልገዋለን። ምቾታችንን ከምንፈልገው በላይ እጅግ አብልጠን እንፈልገዋለን።
እምነት በእግዚአብሔር መታመንና ተአምራትን በእኛ ውስጥ ሲሠራ ማየትን ይወዳል። ስለዚህም እምነት የእግዚአብሔር ጸጋ በኃይልና በነፃነት ወደሚፈስበት የፍቅር ወንዝ ይገፋናል። ጳውሎስ መንፈስን ደስ ለማሰኘት መዝራት አለብን ሲል ይህን እያለ ይመስለኛል (ገላትያ 6፥8)። መንፈስ ቅዱስ እየሠራ መሆኑን ርግጠኛ የሆንንበት የፍቅር እርሻ ላይ በእምነት የጉልበታችንን ዘር መዝራት አለብን። ጊዜውም ሲደርስ መኸሩን እናጭዳለን።