“እንዲሁም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቶአልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ፣ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ” (1ኛ ጴጥሮስ 3፥18)።
የታላቁ የምሥራች ወንጌል ታላቁ ምስራች፣ ከራሱ ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖር ዘላለማዊ ሕብረት ደስ መሰኘታችን ነው። ይህ በ1ኛ ጴጥሮስ 3፥18 “ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ” ተብሎ በግልጽ ተቀምጧል። ኢየሱስም የሞተው ለዚህ ነው።
ሌሎች የወንጌሉ ስጦታዎች የኖሩት ይህንን ታላቅ ስጦታ እውን ለማድረግ ነው።
- በደላችን ከእግዚአብሔር እንዳያርቀን ይቅር ተብለናል።
- ኩነኔአችን ከእግዚአብሔር እንዳያርቀን ጸድቀናል።
- በእኛ እና በእግዚአብሔር አባትነት መካከል ቁጣው እንዳይኖር በራሱ እግዚአብሔር ኀጢአታችን ተሰርዩዋል።
- በእግዚአብሔር በሙላት የመደሰት አቅም እንዲኖረን፣ በትንሣኤ ቀን ከሚነሳ አዲስ አካል ጋር አሁን ላይ የዘላለም ሕይወት ተሰጥቶናል።
እስቲ ልባችሁን መርመሩ። ለምንድነው ይቅርታ የፈለጋችሁት? ለምንስ መጽደቅ ፈለጋችሁ? የእግዚአብሔር ቁጣ እንዲሰረይላችሁ ለምን ጓጓችሁ? የዘላለም ሕይወትን የምትፈልጉት ለምንድን ነው? እውነት ያለ ምንም ጥርጥር፣ አሁንና ለዘላለም በእግዚአብሔር መደሰት ስለምትፈልጉ ነው? የመሻቶቻችሁ ሁሉ መጠቅለያ እና ዋና መሻት በእርግጥ ራሱ እግዚአብሔር ነው?
የእግዚአብሔር ወንጌል የፍቅር ስጦታ በዋናነት ራሱ እግዚአብሔር ነው። የተፈጠርነው ለዚህ ነው። በኀጢአታችንም ያጣነውም ይህንን ነበር። ክርስቶስም የመጣው ይህንን ለመመለስ እና ለማደስ ነው።
“የሕይወትን መንገድ ታሳየኛለህ፤ በአንተ ዘንድ የደስታ ሙላት፣ በቀኝህም የዘላለም ፍሥሓ አለ” (መዝሙር 16፥11)።