የአዲሱ ኪዳን አዲስ ነገር | ሕዳር 28

“ነገር ግን ከዚያ ጊዜ በኋላ፣ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው” ይላል እግዚአብሔር፤ “ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ። እኔ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።” (ኤርምያስ 31፥33)

ኢየሱስ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትዕዛዛትን ከፍቅር አፋቶ መተርጎምን አጥብቆ ይቃወማል።

“ብትወዱኝ ትእዛዜን ትጠብቃላችሁ … የሚወደኝ ትእዛዜን ተቀብሎ የሚጠብቅ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል” ይላል (ዮሐንስ 14፥1521)። “እኔ የአባቴን ትእዛዝ ጠብቄ በፍቅሩ እንደምኖር፣ እናንተም ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ” (ዮሐንስ 15፥10)።

ኢየሱስ ስለ እግዚአብሔር ሕግጋት እና ስለ መታዘዝ ማሰቡ በአባቱ ፍቅር ከመደሰት አላገደውም። እግዚአብሔር አዛዥ መሆኑ ከእርሱ ጋር ያለንን የፍቅር ግንኙነትም እንደማያስተጓጉል እንድናውቅ ይፈልጋል። ፍቅር የሚገለጸው በመታዘዝ ነውና።

ይህን መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር ያለን አዲስ የኪዳን ግንኙነት ትዕዛዛትና ሕግጋት የሌሉት ኪዳን አይደለም። እግዚአብሔር በሙሴ ሕግ በኩል የሠጠው አሮጌው ኪዳን እና በክርስቶስ በኩል የሠጠው አዲስ ኪዳን መካከል ያለው መሠረታዊ ልዩነት፣ አንዱ ትዕዛዛት ያሉት፣ ሌላኛው ግን የሌለው መሆኑ አይደለም።

ዋናዎቹ ልዩነቶች፦ (1) መሲሑ ኢየሱስ መጥቶ የአዲሱን ኪዳን ደም አፍስሷል (ማቴዎስ 26፥28ዕብራውያን 10፥29)። ስለዚህም ከዚያ ጊዜ አንስቶ እርሱ የአዲስ ኪዳን አስታራቂ ነው፤ በዚህም ምክንያት የሚያድነው እና በኪዳን ውስጥ ታማኝነት የሚያጎናጽፈው እምነት፣ በክርስቶስ ላይ ያለ ከልብ የሆነ እምነት ነው። (2) ስለዚህ የቀደመው ኪዳን “አሮጌ” ሆኗል (ዕብራውያን 8፥13)፣ በዚህም ምክንያት የቀደመው ኪዳን የአዲሱን ኪዳን ሕዝብ አይገዛም (2ኛ ቆሮንቶስ 3፥7–18ሮሜ 7፥46ገላትያ 3፥19)። (3) ቃል የተገባው አዲስ ልብ እና የሚያስችለው የመንፈስ ቅዱስ ኅይል በእምነት አማካኝነት ተሰጥተዋል።

እግዚአብሔርን ለመታዘዝ የሚያስችለው ጸጋ ኢየሱስ ከመጣ በኋላ የተገለጠውን ያክል በቀደመው ኪዳን አልተገለጠም ነበር። ዘዳግም 29፥4 እንዲህ ይላል፦ “እስከ ዛሬ ድረስ እግዚአብሔር የሚያስተውል አእምሮ ወይም የሚያይ ዐይን ወይም የሚሰማ ጆሮ አልሰጣችሁም።” በአዲሱ ኪዳን ውስጥ ያለው አዲስ ነገር ትእዛዛት አለመኖራቸው ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል መፈጸሙ ነው! “ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ” ያለው ተፈጽሟል (ኤርምያስ 31፥33)። “መንፈሴን በውስጣችሁ አሳድራለሁ፤ ሥርዐቴን እንድትከተሉና ሕጌን በጥንቃቄ እንድትጠብቁ አደርጋለሁ”(ሕዝቅኤል 36፥27)። እንዳለውም በእርግጥ አድርጓል።