ሌላ ክርስቲያን ሲበድለን | ሐምሌ 6

ለኀጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር እርሱ ራሱ በሥጋው ኀጢአታችንን በእንጨት መስቀል ላይ ተሸከመ፤ በእርሱ ቊስል እናንተ ተፈውሳችኋል።” (1ኛ ጴጥሮስ 2፥24)

ንስሃ ለሚገቡ ክርስቲያን ወንድም እና እህቶቻችን የማናኮርፈው ወይም በደልን የማንቆጥረው በምን መስፈርት ነው?

አስከፊ በደል ያደረሰብን ሰው፣ ክርስቲያን ስለሆነ ብቻ ቁጣችን ይጠፋል ማለት አይደለም። እንዲያውም የበለጠ እንደተከዳን ሊሰማን ይችላል። እንዲያው እንደዋዛ “ይቅርታ” ማለቱ ብቻ፣ ከጥፋቱ ሕመም እና ከበደሉ አስከፊነት ጋር ሲነፃፀር ፍጹም የማይመጣጠን ይመስላል።

ሆኖም ግን፣ አንድ ማስተዋል ያለብን ነገር፣ ይህ ጉዳይ ከአማኝ ባልንጀሮቻችን ጋር መሆኑ ነው። የእግዚአብሔር ቁጣ ደግሞ በእነርሱ ላይ አይሰራም፤ ምክንያቱም “በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም” ይላል (ሮሜ 8፥1)። ደግሞም በተጨማሪ፣ “እግዚአብሔር ድነትን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንድናገኝ ነው እንጂ ለቍጣ ወስኖ አላስቀመጠንምና” ይላል (1ኛ ተሰሎንቄ 5፥9)። በቃ አመለጡ ማለት ነው?

ታዲያ ወዴት እንዙር? ክርስትና በኃጢአት ክብደት ላይ የሚሳለቅ እንዳልሆነና በእርግጥ ፍትሕ እንደሚሰፍን ርግጠኛ ለመሆን ወዴት እንመልከት?

መስቀሉን እንመልከት! በእውነተኛ ክርስቲያን ወንድም እህቶቻችን የደረሰብን በደል ሁሉ በክርስቶስ ሞት ተከፍሏል። ቀላል በሚመስል ነገር ግን አስደናቂ በሆነ ጥቅስ ውስጥ ይህንን መልስ እናገኛለን። የእግዚአብሔር ልጆች ኃጢአት ሁሉ በኢየሱስ ላይ ተከምሮ ኢየሱስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሞቶ ከፍሎታል። “እግዚአብሔርም፣ የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ ጫነው” (ኢሳይያስ 53፥61 ጴጥሮስ 2፥24)።

የክርስቶስ መከራ ክርስቲያን ባልንጀሮቻን ላደረሱብን ጉዳትና በደል ሁሉ የእግዚአብሔር እውነተኛ የሆነ ቅጣትና ማወራረጃ ክፍያ ነው። ስለዚህ ክርስትና ኃጢአትን ቀላል አያደርግም። ጉዳታችንም ላይ ስድብን አይጨምርም።

በተቃራኒው፣ በእኛ ላይ የተፈጸመውን ኃጢአት አክብዶ ይመለከተዋል። የደረሱብንን በደሎች እና ጉዳቶች ለማስተካከል፣ የበደሉንን ልንበቀላቸው ከምንችለው በላይ እንዲሠቃይ እግዚአብሔር የገዛ ልጁ አሳልፎ ሰጥቷል። በሚያምኑ ባልንጀሮቻችን ላይ ቂም የምንይዝ ከሆነ፣ የክርስቶስ መስቀል ለእግዚአብሔር ሕዝብ ኃጢአት በቂ ክፍያ አይደለም እያልን ነው። ይህ ደግሞ ክርስቶስንና መስቀሉን መሳደብ ነው።