በተከሰስሁበት ነገር የመጀመሪያ መከላከያዬን ሳቀርብ ማንም ሊያግዘኝ አልመጣም፤ ነገር ግን ሁሉ ትተውኝ ሄዱ። ይህንም አይቍጠርባቸው። ነገር ግን መልእክቱ በእኔ አማካይነት በሙላት እንዲሰበክና አሕዛብ ሁሉ እንዲሰሙት ጌታ በአጠገቤ ቆሞ አበረታኝ፤ ከአንበሳም መንጋጋ አዳነኝ። ጌታ ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል፤ ወደ ሰማያዊው መንግሥቱም በሰላም ያደርሰኛል፤ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን። (2ኛ ጢሞቴዎስ 4፥16-18)
ዛሬ ማለዳ እነዚህን ጣፋጭ እና ልብ ሰባሪ ቃላት እያሰብኩ ነበር። ጳውሎስ በሮም ታስሮ ነበር፤ እስከምናውቀው ድረስ አልተለቀቀም። እናም የመጨረሻ ደብዳቤው በዚህ መልኩ ነበር ያለቀው።
አስቡት እና ይግረማችሁ!
ብቻውን ቀርቶ ነበር፦ “ማንም ሊያግዘኝ አልመጣም“ አለ። ታማኝ አገልጋይ ቢሆንም አርጅቶ ነበር። በዚያ ላይ ከቤቱ በጣም በሚርቅ ከተማ በሞት አደጋ ውስጥ ነበር። ለምን? ምናልባትም ብቸኛ እና በፍርሃት ለተሞላን ለእኛ ይህንን ቃል ይጽፍ ዘንድ ይሆናል፦ “ጌታ በአጠገቤ ቆሞ አበረታኝ።”
እነዚህን ቃላት እንዴት እንደምወዳቸው! ጓደኞቻችሁ ጥለዋችሁ ሲሄዱ በእግዚአብሔር ላይ ታማርራላችሁ? ታዲያ እነዚህ ሰዎች አምላኮቻችሁ ናቸው ማለት ይሆን? ወይስ “… እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” በሚለው አስደናቂ የተስፋ ቃል ትታመናላችሁ (ማቴዎስ 28፥20)? ሁሉም ጥለዋችሁ ቢጠፉ እና ብቻችሁን ብትተዉ፣ “ከቶ አልተውህም፤ በፍጹም አልጥልህም” በሚለው ጽኑ ቃል ኪዳን ልባችሁን ታጠነክራላችሁ (ዕብራውያን 13፥5)?
ስለዚህም “ጌታ በአጠገቤ ቆሞ አበረታኝ!” እንበል!
እስቲ አንዳንድ ጥያቄዎች እንመልከት፦
ጥያቄ፦ በ2ኛ ጢሞቴዎስ 4፥18 ላይ ያለው ማስፈራሪያ ምን ነበር? መልስ፦ ጳውሎስ መንግሥተ ሰማይን ላይወርስ ይችላል የሚል ነበር! ነገር ግን ለነበረበት ከባድ ሁኔታ እንዲህ አለ፦ “ወደ ሰማያዊው መንግሥቱም በሰላም ያደርሰኛል።”
ጥያቄ፦ ጳውሎስ መንግሥተ ሰማይ ላይገባ ይችል የነበረው እንዴት ነው? መልስ፦ በክፉ ነገር አማካኝነት፦ “ጌታ ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል፤ ወደ ሰማያዊው መንግሥቱም በሰላም ያደርሰኛል።”
ጥያቄ፦ እንዴት ነው ጳውሎስ መንግሥተ ሰማይ እንዳይገባ ክፉው ነገር ሊያደርገው የሚችለው? መልስ፦ ለክርስቶስ እንዳይታዘዝ በማድረግ፣ ጌታውን በማስካድ።
ጥያቄ፦ ታዲያ ይህ ፈተና ከአንበሳው መንጋጋ መዳኑ ነበር? መልስ፦ በትክክል! “ራሳችሁን የምትገዙ ሁኑ፤ ንቁም፤ ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ ወዲያ ወዲህ ይዞራል። በዓለም ዙሪያ ያሉት ወንድሞቻችሁ ተመሳሳይ መከራ እንደሚቀበሉ ዐውቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት” (1ኛ ጴጥሮስ 5፥8-9)።
ጥያቄ፦ ታዲያ ጳውሎስ በዚህ ፈተና ስላልወደቀ እና በእምነት እና ታዛዥነት ስለቀጠለ ክብሩን የሚወስደው ማነው? መልስ፦ “ኀይል ከዘላለም እስከ ዘላለም ለእርሱ ይሁን፤ አሜን“ (1ኛ ጴጥሮስ 5፥10)። “ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን” (2ኛ ጢሞቴዎስ 4፥18)።
ጥያቄ፦ ቆይ ለምን? ጳውሎስ ጠንክሮ የቆመው በራሱ አልነበረምን? መልስ፦ በፍጹም! “ጌታ በአጠገቤ ቆሞ አበረታኝ!”