. . . እኛ ሁላችን በአንድ ወቅት የሥጋችንን ምኞት እያረካን፣ መንገዱንም እየተከተልን በመካከላቸው እንኖር ነበር፤ እንደ ሌሎቹም የቍጣ ልጆች ነበርን። (ኤፌሶን 2፥3)
ለእኛ ይገባ የነበረው የእግዚአብሔር ቁጣና ኩነኔ ሁሉ በኢየሱስ ላይ ወረደ። እግዚአብሔር የሚፈልገው ፍጹም የሆነ ጽድቅ በኢየሱስ ተፈጸመ። በጸጋ፣ ይህንን የከበረ እውነት በመረዳት ስንቀበለው፣ የእርሱ ሞት ሞታችን፣ ኩነኔውም ኩነኔያችን እንዲሁም ጽድቁ ጽድቃችን ሆኖ ይቆጠራል። በዚያም ቅጽበት ድጋሚ ላይሻር፣ እግዚአብሔር ለዘላለም ለእኛ ይወግናል።
ይህም “መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ከዘላለም በፊት በምርጫው ሞገሱን እንደሰጠን አያስተምርም ወይ?” የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል።
በሌላ አነጋገር፣ ይህን በደንብ ስናስበው፣ “እግዚአብሔር ለእኛ የወገነው ወደእምነት በመጣንበት እና ከክርስቶስ ጋር ህብረት በማድረግ በጸደቅንበት ቅጽበት ነው? ወይስ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በምርጫው ለእኛ ወግኗል?” ብለው እንጠይቃለን። ጳውሎስም በኤፌሶን 1፥4-5 ላይ እንዲህ ይላል፦ “በፊቱ ቅዱሳንና ነውር አልባ እንድንሆን ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ በእርሱ መርጦናልና። በፍቅር፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ልጆቹ እንሆን ዘንድ፣ እንደ በጎ ፈቃዱ አስቀድሞ ወሰነን።”
እንግዲያስ እግዚአብሔር ለምርጦቹ ከዘላለም በፊት አልወገነም ነበር ማለት ነው? መልሱ 100% በሚለው ውስጥ ይገኛል።
“100%” በሚለው አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ቦታ ላይ የተጠቀሱ እውነታዎችን ለመጠበቅ እንሞክራለን። ለምሳሌ፣ በኤፌሶን 2፥3 ላይ፣ ጳውሎስ ክርስቲያኖች በኢየሱስ ክርስቶስ ሕያዋን ከመሆናቸው በፊት “የቁጣ ልጆች” እንደነበሩ ይናገራል። “እኛ ሁላችን በአንድ ወቅት የሥጋችንን ምኞት እያረካን፣ መንገዱንም እየተከተልን በመካከላቸው [ለእግዚአብሔር በማይታዘዙት ሰዎች] እንኖር ነበር፤ እንደ ሌሎቹም የቍጣ ልጆች ነበርን።”
ጳውሎስ እያለ ያለው፣ ዳግም ከመወለዳችን በፊት፣ ማለትም ከክርስቶስ ጋር ሕያዋን ከመሆናችን በፊት የእግዚአብሔር ቁጣ በላያችን ላይ ነበር ነው። የተመረጡት በቁጣ ስር ነበሩ። ይህም የተቀየረው እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ ሕያዋን ሲያደርገን እና እውነትን እና የክርስቶስን ውብት እንድናይ ሲያነቃን ነው። ስለዚህም ከእርሱ ጋር አንድ በመሆናችን ለእኛ እንደሞተልን እና የእርሱም ጽድቅ ለእኛ እንደተቆጠረ በማመን ተቀበልነው። ይህ ለእኛ ከመሆኑ በፊት፣ በእግዚአብሔር ቁጣ ሥር ነበርን። ከዚያ ግን፣ ክርስቶስን በማመንና ከእርሱም ጋር አንድ በመሆን የእግዚአብሔር ቁጣ ሁሉ ከእኛ ተወገደ። በዚያ መልኩም እርሱ 100% ለእኛ ወገነ።
ስለዚህም፣ እግዚአብሔር እንደሚያጸናችሁ በማወቅ ሐሴትን አድርጉ። እርሱ በክርስቶስ በኩል ለእናንተ 100% ስለወገነ፣ እስከ ፍጻሜው ያደርሳችኋል። እግዚአብሔር ለእናንተ የሚወግነው ወደ ፍጻሜው ስለምትደርሱ አይደለም። ወደ ፍጻሜው የምትደርሱት እርሱ ለእናንተ መቶ በመቶ ስለወገነ ነው።