ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ስለ ፈለገ፣ ልጆቹ የአባታቸውን ተግሣጽ አልሰሙም። (1ኛ ሳሙኤል 2፥25)
የካህኑ ኤሊ ልጆች በኃጢአታቸው ምክንያት አባታቸው በገሰጻቸው ጊዜ አልሰሙትም። ታዲያ ከዚህ ክፍል ለሕይወታችን የሚሆኑ ሦስት ትምህርቶችን መውሰድ እንችላለን፦
- ሆን ተብሎ ለረጅም ጊዜ በሚሰራ ክፉ የኃጢአት ልምምድ የተነሣ ጌታ ንሰኀን ሊከለክል ይችላል።
ለዚህ ነው ጳውሎስ፣ ከዚህ ሁሉ ልመናና ትምህርት በኋላ ‘እግዚአብሔር ንስሓን እንደሚሰጣቸው ተስፋ በማድረግ’ ብሎ የተናገረው (2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥25)። ‘ንሰሃን በእርግጥ ይሰጣቸዋል’ አለማለቱን አስተውሉ። በኃጢአት ልምምድ ሕይወት ውስጥ “ማርፈድ” የሚባል ነገር አለ። በዕብራውያን 12፥17 ላይ ስለ ዔሳው እንደተፃፈው ማለት ነው፦ “በረከቱን በእንባ ተግቶ ቢፈልግም መልሶ ሊያገኘው አልቻለም።” እግዚአብሔር ትቶታልና ንሰሓ መግባት አልቻለም።
ይህ ማለት ሕይወታቸውን በሙሉ በኅጢአት ልምምድ ውስጥ ከኖሩ በኋላ ከልባቸው ንሰሓ የሚገቡ ሰዎች አይድኑም ማለት አይደለም። መዳን ይችላሉ፤ ደግሞም ይድናሉ። እግዚአብሔር የሚደንቅ መሐሪ አምላክ ነው። ከኢየሱስ አጠገብ የተሰቀለውን ሌባ አስታውሱት። ኢየሱስ እንዲህ ብሎት ነበር፦ “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” (ሉቃስ 23፥43)።
- አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር በኃጢአት ልምምድ ውስጥ ያለን ሰው ትክክለኛውን ነገር ከማድረግ ሊከለክለው ይችላል።
“ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ስለ ፈለገ፣ ልጆቹ የአባታቸውን ተግሣጽ አልሰሙም።” የአባታቸውን ተግሣጽ መስማት፣ ሊያደርጉት የሚገባቸው ትክክለኛው ነገር ነበር። ነገር ግን አላደረጉትም። ለምን? ክፍሉ፣ “እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ስለፈለገ” ይለናል።
አባታቸውን ላለመታዘዛቸው የተሰጠው ምክንያት፣ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የነበረው ሌላ ዕቅድ ነው። ይህ የሚያሳየን አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር በሉዓላዊ ዕቅዱ መሠረት የሚፈቅደው ነገር፣ በቃሉ ከተገለጠው ፈቃዱ ጋር የተለየ ሊሆን እንደሚችል ነው።
- አንዳንድ ጊዜ እንደ እግዚአብሔር ሃሳብ የጸለይናቸው ጸሎቶቻችን የማይመለሱልን፣ እግዚአብሔር ቅዱስና ጠቢብ ለሆነው ዕቅዱ ሲል በተለየ መንገድ ስለሚጓዝ ነው።
ኤሊ ልጆቹ ወደ መልካም እንዲለወጡ ጸልዮ ነበር ብለን እንገምታለን። ትክክለኛ ጸሎትም ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር አፍኒን እና ፊንሐስ እንዲታዘዙ ሳይሆን እንዲሞቱ ወስኗል።
እንደነዚህ ዐይነት ሊገመቱ የማይችሉ ነገሮች ሲፈጠሩና እግዚአብሔር እንዲቀይራቸው በእንባ ወደ እርሱ ስንጮህ፣ የእግዚአብሔር መልስ፣ “እንቢ፣ አልወዳችሁም!” የሚል አይደለም። ይልቁንም፣ የእርሱ ምላሽ፣ “ለዚህ ኃጢአት ንሰሃን የማልሰጥበት ቅዱስና ጠቢብ ምክንያት አለኝ። አሁን ልታዩት እና ልትረዱት የማትችሉት፣ እኔ ግን በዕቅዴ መሠረት የምሰራቸው ሥራዎች አሉኝ። እመኑኝ። የማደርገውን አውቃለሁ። እወዳችኋለሁ” የሚል ነው።