እግዚአብሔር ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ፣ የሚምልበት ከእርሱ የሚበልጥ ሌላ ባለመኖሩ፣ በራሱ ማለ፤ እንዲህም አለ፤ “በርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህንም አበዛዋለሁ።” (ዕብራውያን 6፥13–14)
ዋጋው፣ ክብሩ፣ ማዕረጉ፣ ውድነቱ፣ ትልቅነቱ፣ ውበቱና ዝናው ከሌሎች የከበሩ ነገሮች ጥርቅም ይልቅ አሥር ሺህ ጊዜ የሚበልጥ አንድ ማንነት አለ፦ እርሱም ራሱ እግዚአብሔር ነው። ስለዚህ፣ እግዚአብሔር መሀላ ሲፈጽም በራሱ ይምላል።
ተስፋ ባደረጋችሁት ነገር ላይ ጽኑ ማረጋገጫን ለመስጠት ሲል፣ ከራሱ ስም ከፍ ያለ ነገር ቢኖር ኖሮ በዚያ ይምል ነበር። እግዚአብሔር በራሱ ሲምል እያለ ያለው ነገር፣ ራሱን ሊጠላ እንደማይቻለው ሁሉ፣ እኛን ለመባረክ የገባውን የተስፋ ቃል ማጠፍ እንደማይችል ነው።
እግዚአብሔር በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ ያለው ትልቁ ውድ ነገር ነው። ከእግዚአብሔር የበለጠ ውድና ድንቅ ነገር የለም። ስለዚህ እግዚአብሔር በእግዚአብሔር ይምላል። ይህንንም ሲያደርግ፣ “በእኔ ላይ ሊኖርህ የሚችለውን መተማመን ሁሉ እንዲኖርህ ነው” እያለ ነው። የሚምልበት የተሻለ ነገር ቢኖር ኖሮ ያንን ይሰጠን እንደነበር ቃሉ ይነግረናል። “የሚምልበት ከእርሱ የሚበልጥ ሌላ ባለመኖሩ፣ በራሱ ማለ” (ዕብራውያን 6፥13)።
ይህ ነው አምላካችን። የማይናወጥ ተስፋችሁ በእርሱ ላይ በመሆኑ እንድትተማመኑ፣ ሊታሰብ በሚችለው ታላቁ ከፍታ ላይ የማለ አምላክ ነው። ስለዚህ፣ መሸሸጊያ ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር ሽሹ። ፋይዳ ቢስ እና አታላይ ከሆኑ የዓለም ተስፋዎች አምልጡና ተስፋችሁን በእግዚአብሔር ላይ አድርጉ። ከእግዚአብሔር የተሻለ መሸሸጊያና የተስፋ አለት የሚሆን ምንም እና ማንም የለም።