“ባሎች ሆይ፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ፣ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በቃሉ አማካይነት በውሃ አጥቦ በማንጻት እንድትቀደስ፣…ለራሱ ክብርት ቤተ ክርስቲያን አድርጎ ሊያቀርባት ነው” (ኤፌሶን 5፥25-26)።
ከእግዚአብሔር ለማግኘት ተሰፋ የምታደርጉት ቅድመ ሁኔታ የሌለው ፍቅር ብቻ ከሆነ፣ ተስፋችሁ ታላቅ ነው፣ ነገር ግን አሁንም ቢሆን ትንሽ ነው።
እግዚአብሔር እኛን ያለ ምክንያት መውደዱ ብቻውን የፍቅሩን ጣፋጭነት አያሳይም። የፍቅሩ ጣፋጭነት የሚቀመሰው እንዲህ ሲለን ነው፦ “ልጄን እንድትመስሉ ስላደረግኋችሁ፣ እናንተን ማየት እና አብሬአችሁ መሆን እጅግ ያስደስተኛል። ክብሬን ስለምታንጸባርቁ እናንተ ደስታዬ ናችሁ።”
እግዚአብሔርን በምርጫችን እና በተግባራችን ለማስደስት የምንፈልግ ሰዎች እንድንሆን፣ ይህ ጣፋጭ ልምምድ አስፈላጊ ነው።
ቅድመ ሁኔታ የሌለው ፍቅር የሰውን ልጅ ከሥር መሠረቱ ለመለወጥ ኀይል አለው። ይህም ኀይል ቅድመ ሁኔታ ላይ ለተመሰረተው ፍቅር ምንጭ እና መሠረት መሆን የሚችል ነው። እግዚአብሔር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ባይወደን ኖሮ፣ ወደቆሻሻው ሕይወታችን ገብቶ ወደ እምነት ባላመጣን ነበር፤ እንዲሁም ከክርስቶስ ጋር አንድ ባላደርገን፣ መንፈሱንም ባልሰጠንና ቀስ በቀስም ክርስቶስን ወደ መምስል ባልቀየረን ነበር።
ነገር ግን ያለ ቅድመ ሁኔታ ሲመርጠን፣ ክርስቶስ ለእኛ እንዲሞት ሲልክልን እና ዳግም ሲወልደን፣ ሊቋረጥ የማይችለውን የምንከብርበትን የለውጥ ሂደት አስጀምሯል። በዚህም ሂደት ውስጥ እርሱ የሚወደውን ዐይነት ውበት ይሰጠናል፤ ይህም የልጁን መልክ የሚመስለው ነው።
ይህንን በኤፌሶን 5፥25-27 ውስጥ እናያለን። “ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ [ቅድመ ሁኔታ የሌለው ፍቅር]፣ … በቃሉ አማካይነት በውሃ ዐጥቦ በማንጻት እንድትቀደስ፣ እንዲሁም ጕድፍ ወይም የፊት መጨማደድ ወይም አንዳች እንከን ሳይገኝባት ቅድስትና ነውር አልባ የሆነች ክብርት ቤተ ክርስቲያን አድርጎ ለራሱ ሊያቀርባት ነው።” ያለ ቅድመ ሁኔታ ወደዳት፣ ከዚያም እርሱ የሚደሰትባትን ቅድመ ሁኔታዎች እንድታሟላ አደረጋት።
የማያምኑ ኀጢአተኞች ሳለን እግዚአብሔር ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ፍቅሩን በእኛ ላይ ማድረጉ ሊገለጽ የማይችል ድንቅ ነገር ነው። ይህ ድንቅ የሆነበት ዋነኛው ምክንያት ይህ ቅድመ ሁኔታ የሌለው ፍቅሩ ወደ ዘላለማዊ የክብሩ መገኘት ደስታ ስለሚያደርስን ነው።
ነገር ግን የዚያ ደስታ ጣሪያ እኛ የእርሱን ክብር ማየታችን ብቻ ሳይሆን ማንጸባረቃችንም ነው። ይህንንም በ2ኛ ተሰሎንቄ 1፥12እናነብባለን፦ “የጌታችን የኢየሱስ ስም በእናንተ ዘንድ እንዲከብርና እናንተም በእርሱ እንድትከብሩ ይህን እንጸልያለን።”