በጭንቀቴ ጊዜ | ሕዳር 9

. . . እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። (1ኛ ጴጥሮስ 5፥7)

ለምትፈተኑበት ለእያንዳንዱ ኅጢአት እና ልባችሁን በቅጽበት ወርሮ፣ ክፉኛ ለሚያስጨንቃችሁ አለማመን የሚሆኑ የተስፋ ቃሎች አሉ። ለአብነት ያህል እነዚህን ተመልከቱ።

ስለ መታመም ስጨነቅ፣ አለማመንን “የጻድቅ መከራው ብዙ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ከሁሉም ያድነዋል” በሚለው የተስፋ ቃል እዋጋለሁ (መዝ. 34፥19)። እናም “በዚህ ብቻ ሳይሆን በመከራችንም ሐሤት እናደርጋለን፤ ምክንያቱም መከራ ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን። ትዕግሥት ጽናትን፣ ጽናት የተፈተነ ባሕርይን፣ የተፈተነ ባሕርይ ተስፋን፤ ይህም ተስፋ ለዕፍረት አይዳርገንም፤ እግዚአብሔር በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ ፍቅሩን በልባችን አፍስሶአልና” የሚለውን ተስፋ በመንቀጥቀጥ እቀበለዋለሁ (ሮሜ 5፥3-5)።

ማርጀቴን እያሰብኩ ስጨነቅ፣ አለማመንን “እስከ ሽምግልናችሁ፣ እስከ ሽበትም፣ የምሸከማችሁ እኔ ነኝ፤ እኔው ነኝ። ሠርቻችኋለሁ፤ እሸከማችኋለሁ፤ እደግፋችኋለሁ፤ አድናችኋለሁ” በሚለው የተስፋ ቃል እዋጋለሁ (ኢሳይያስ 46፥4)።

ስለ መሞት ስጨነቅ፣ ከአለማመን ጋር የምዋጋው በዚህ የተስፋ ቃል ነው፦ “ከእኛ ማንም ለራሱ የሚኖር፣ ለራሱም የሚሞት የለምና። ብንኖር ለጌታ እንኖራለን፤ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን፤ ስለዚህ ብንኖርም ብንሞትም የጌታ ነን። ለዚሁ፣ የሙታንና የሕያዋን ጌታ ይሆን ዘንድ ክርስቶስ ሞቶአል፤ በሕይወትም ተነሥቶአል” (ሮሜ 14፥7-9)።

እምነቴ እንደመርከብ ተሰባብሮ ይሰጥም ይሆን እያልኩ፣ ከእግዚአብሔር መራቅን እያሰብኩ ስጨነቅ እና ስጠበብ፣ “በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እርሱ እስከ ክርስቶስ ኢየሱስ ቀን ድረስ ከፍጻሜው እንደሚያደርሰው ርግጠኛ ነኝ” በሚለው ቃል እና፣ “ስለዚህ ስለ እነርሱ እየማለደ ሁል ጊዜ በሕይወት ስለሚኖር፣ በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል” በሚለው ጥቅስ አለማመንን እዋጋለሁ (ፊልጵስዩስ 1፥6) (ዕብ. 7፥25)።

ስለዚህ ጦርነትን፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሳይሆን ከራሳችን አለማመን ጋር እናድርግ። አለማመን የጭንቀት ሁሉ ሥር ነው፤ ሌሎችም ብዙ ኅጢአቶች ከዚሁ ይመዘዛሉ።

እንግዲያውስ፣ ዐይኖቻችንን በእግዚአብሔር ውድና እጅግ ታላቅ የተስፋ ቃሎች ላይ እናድርግ። መጽሐፍ ቅዱሳችሁን አንሱ፤ መንፈስ ቅዱስ እንዲረዳችሁ ለምኑት፤ የተስፋ ቃሎቹን በልባችሁ አኑሩ፤ መልካሙን ገድል ተጋደሉ። ወደፊት ሊገለጥ ባለው ጸጋ ውስጥ በእምነት ኑሩ።