ሰነፍ፣ “አንበሳ ውጭ አለ፤ መንገድ ላይ እገደላለሁ” ይላል። (ምሳሌ 22፥13)
ምሳሌው ይላል ብዬ ያሰብኩት ይህንን አልነበረም። “ፈሪ፣ ‘አንበሳ ውጭ አለ፤ መንገድ ላይ እገደላለሁ’ ይላል” እንዲል ጠብቄው ነበር። ነገር ግን የሚለው “ሰነፍ” እንጂ “ፈሪ” አይደለም። ስለዚህ፣ እዚህ ጋር ተቆጣጣሪው ስሜት፣ ስንፍና እንጂ ፍርሃት አይደለም።
ታዲያ ግን ስንፍናን እና በመንገድ ላይ ያለ የአንበሳ አደጋን ምን አገናኛቸው? መቼም አብዛኛውን ጊዜ፣ “ይህ ሰውዬ አንበሳ ውጪ አለ ብሎ ስራውን ለመስራት እጅግ ሰንፏል” አንልም።
ምን እያለ ነው? ሰነፍ ሰው ሥራ ላለመስራቱ ማመካኛ ለማቅረብ ምናባዊ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። ከዚያም የሁሉንም ትኩረት ከስንፍና በሽታው አንስቶ ወደ አንበሶች ያዞረዋል። ቀኑን ሙሉ ቤት የሚቀመጠው በስንፍናው ብቻ ከሆነ ማንም አይቀበለውም። ግን መንገድ ላይ አንበሳ አለ ካለ፣ አሳማኝ ምክንያት ሊመስልለት ይችላል።
ከዚህ ልንማር የሚገባን መሠረታዊ የሆነ አንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት፣ ልባችን የሚፈልገውን ነገር ለማግኘት ማሳበቢያ የሚወስደው አእምሮአችንን በመጠቀም እንደሆነ ነው። ይህ ማለት፣ ጥልቅ ምኞቶቻችን፣ ጥሩም ሆኑ መጥፎ፣ ከአእምሯችን ምክንያታዊ አሠራር ይቀድማሉ። አዕምሯችን እነዚህን ምኞቶች የሚረዳው ተገቢ እንደሆኑ ፍላጎቶች አድርጎ ነው።
ሰነፍም ሰው የሚያደርገው ይህንኑ ነው። አለመሥራትን እና ቤት መጎለትን ከልቡ ይፈልጋል። ነገር ግን ሥራ ፈትቶ ቤት ለመቀመጥ ጥሩ ምክንያት ያስፈልጋል። ስለዚህ ምን ያደርጋል? ክፉውን የስንፍና ፍላጎቱን ያሸንፋል? አያሸንፍም። ይልቁንም ለምኞቱ ማመካኛ ለማቅረብ፣ አእምሮውን በመጠቀም ምናባዊ አደጋዎችን ይፈጥርና ለዚህ ነው ቤት ቁጭ ያልኩት ይላል።
ኢየሱስ፣ “ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለ ነበረ፣ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ” ብሎ ተናግሯል (ዮሐንስ 3፥19)። ጨለማን የምንወደው ማድረግ የፈለግነውን ሳንጋለጥ ማድረግ ስለሚያስችለን ነው። አዕምሯችን ደግሞ የልባችን ክፉ ምኞት እንዳይጋለጥና እንዳይጠፋ ለመጠበቅ ሲል ጨለማ የሚያመርት ፋብሪካ ይሆናል። ዕለት ዕለት ግማሽ እውነት፣ ውሸት፣ ማጭበርበር እና ክህደት በዓይነት በዓይነት ያመርታል።
ይህንን ልብ በሉ። አስተዋይ ሁኑ።