ሸክላ ሠሪው ለእኛ ሲሆን | መጋቢት 12

“ከዐፈር ሸክላዎች መካከል፣ ከሠሪው ጋር ክርክር ለሚገጥም ወዮለት! ጭቃ፣ ሸክላ ሠሪውን፣ ‘ምን እየሠራህ ነው?’ ይለዋልን? የምትሠራውስ ሥራ፣ ‘እጅ የለህም’ ይልሃልን? (ኢሳይያስ 45፥9)

የእግዚአብሔር ክብር የሚጎላው በፈጣሪነቱ ስንመለከተው ነው። ከምንም ነገር በትዕዛዝ መፍጠር የሚችል ነውና።

ጭቃውን ከምንም ይፈጥረዋል፤ ከጭቃውም እኛን ይሠራናል። እኛ ደግሞ የጌታ የሸክላ እቃዎች ነን (ኢሳይያስ 45፥9)፤ ሙሉ በሙሉ በእርሱ ላይ ጥገኛ የሆንን የክብሩ እቃዎች ነን።

“እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን ዕወቁ! እርሱ ፈጠረን፤ እኛም የእርሱ ነን፤ እኛ ሕዝቡ የማሰማሪያው በጎች ነን“ (መዝሙር 100፥3)። የሌላ ሰው በግ እና ሸክላ ከመሆን በላይ ትሑት የሚያደርግ ነገር የለም።

ዛሬ ጠዋት ኢሳይያስን ሳነብ አንድ ሌላ የእግዚአብሔርን ክብር የሚገልጽ ጽሑፍ አገኘሁ። ከእግዚአብሔር እንደ ፈጣሪ ካለው ሙሉ ኅይል እና መብት ጋር ሳገናኘው ልቤ ተቃጠለ!

“እግዚአብሔር በዚያ ኀይላችን ይሆናል!“ (ኢሳይያስ 33፥21)።

ፈጣሪ ለእኛ እንጂ በእኛ ላይ አይደለም። በዓለማት ሁሉ ላይ በሚሠራው ኅይሉ እንደፈለገ ማድረግ ሲችል፣ ለእኛ እና ከእኛ ጋር ቆመ!

“ከጥንት ጀምሮ፣ በተስፋ ለሚጠባበቁት የሚደርስላቸው፣ እንደ አንተ ያለውን አምላክ ያየ ዐይን፣ ያደመጠ ጆሮ ፈጽሞ አልነበረም” (ኢሳይያስ 64፥4)። “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ፣ ማን ሊቃወመን ይችላል?“ (ሮሜ 8፥31)።

እግዚአብሔር ለእኛ ነው ከማለት በላይ ምን የሚያጽናና እና የሚያስደስት ነገር አለ?