መቼ ይሆን የምረካው? | ሐምሌ 3

ለእኔ ያለህ ፍቅር በእነርሱ እንዲሆን፣ እኔም በእነርሱ እንድሆን፣ አንተን እንዲያውቁ አድርጌአለሁ፤ እንዲያውቁህም አደርጋለሁ።” (ዮሐንስ 17፥26)

በዓለም ላይ ካሉ ደስታዎች እና እርካታዎች ሁሉ የሚልቀውን እርካታ ያለ ምንም ክልከላ፣ እየጨመረ በሚሄድ ስሜትና ጉልበት ለዘለዓለም ማጣጣም ቢቻል ብላችሁ ለአፍታ አስቡ።

መቼም ይሄ የማናችንም ተሞክሮ ወይም ልምድ አይደለም። ሁሌም ቢሆን፣ በዚህ ዓለም ውስጥ ሊኖረን ከሚችል ፍፁም እርካታ እንቅፋት ሆነው የሚቆሙ ሦስት ነገሮች አሉ፦

  1. በዚህ ዓለም ውስጥ፣ የልባችንን ጥልቅ ምኞትና ረሃብ ለማሟላት የሚችል ምንም ነገር የለም።
  2. እጅግ ውድ የሆኑ እርካታዎችን በሚመጥናቸው ልክ የማጣጣም አቅም ይጎድለናል።
  3. በዚህ ምድር እስካለን ድረስ፣ በነገሮች ላይ ያለን ደስታ ወዲያውኑ ያልቃል፤ ምንም ነገር ዘላቂ አይደለም።

ነገር ግን በዮሐንስ ወንጌል 17፥26 ላይ ያለው የኢየሱስ ዓላማና ግብ ከተፈጸመ ይሄ ሁሉ ነገር ይለወጣል። ስለ እኛ ወደ አባቱ እንዲህ ሲል ጸልዩዋል፦ “ለእኔ ያለህ ፍቅር በእነርሱ እንዲሆን፣ እኔም በእነርሱ እንድሆን፣ አንተን እንዲያውቁ አድርጌአለሁ፤ እንዲያውቁህም አደርጋለሁ።” እግዚአብሔር ልጁን የሚወድደው ኀጢአተኞችን በሚወድበት መንገድ አይደለም። ልጁን የሚወድደው ዘላለማዊ ፍቅር የሚገባው ስለሆነ ነው። ልጁ ወሰን አልባ የሆነ ተወዳጅነት ያለው ልጅ ነው። ይህ ማለት ይህ ፍቅር ሙሉ በሙሉ ጣፋጭ እና አስደሳች ነው ማለት ነው። እናም፤ ልክ እግዚአብሔር በልጁ እንዳለው ደስታ እና እርካታ እኛም በኢየሱስ ላይ ይኖረን ዘንድ ጸልዮልናል።

እግዚአብሔር አብ በልጁ ያለው ደስታ የእኛም ደስታ ከሆነ፤ ደስታችን የሆነው ኢየሱስ ተወዳዳሪ የሌለው እጅግ ውድ ወዳጅ ይሆንልናል ማለት ነው። መቼም ቢሆን አያስከፋንም፣ አይሰለቸንም፣ አይበድለንም፣ ወይም አይደብረንም። ከእግዚአብሔር ልጅ ከኢየሱስ ክርስቶስ በላይ ውድ የሆነ ሃብት አይታሰበንም።

ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ፣ ይህንን ወሰን አልባ የሆነውን ክቡር ሃብት የማጣጣም አቅማችን፣ ጉልበታችንና ስሜታችን በሰዋዊ ድክመቶች እንዳይገደብ ኢየሱስ ፀልዮልናል። ሁሉን ቻይ በሆነው በአባቱ ደስታ ልክ፣ የእግዚአብሔርን ልጅ ደስ እንሰኝበታለን። ይህ ምነኛ አስደሳች ተስፋ ነው? እግዚአብሔር በልጁ ያለው ያው ደስታ በውስጣችን ይኖራል፣ ማንም ላይወስድብን ለዘላለም ይሰጠናል። አብ እና ወልድ ፍፃሜ ስለሌላቸው ይህም ደስታ ፍፃሜ አይኖረውም። እርስ በእርስ ያላቸው ፍቅር እኛ ለእነርሱ ከሚኖረን ፍቅር ጋር አንድ ስለሚሆን፤ ለእነርሱ ያለን ፍቅር ለዘላለም አይበርድም፣ አይጠፋምም።