የማትሞቱ ስትሆኑ | የካቲት 19

በነጋም ጊዜ አይሁድ ተሰባስበው በማሤር ጳውሎስን እስኪገድሉት ድረስ እህል ውሃ ላለመቅመስ ተማማሉ። (ሐዋሪያት 23፥12)

ጳውሎስን እስከሚገድሉት ድረስ አንበላም ብለው ቃል ስለገቡት ረሃብተኞች ምን ማለት እንችላለን?

በሐዋሪያት ሥራ 23፥12 ላይ ስለ እነርሱ እናነባለን፦ “በነጋም ጊዜ አይሁድ ተሰባስበው በማሤር ጳውሎስን እስኪገድሉት ድረስ እህል ውሃ ላለመቅመስ ተማማሉ” ይላል። ነገር ግን አልተሳካላቸውም። ለምን? ተያያዥ የሆኑና ያልታሰቡ ክስተቶች ተፈጥረው ነበር።

     

      • አንድ ልጅ ይህን ሴራ ይሰማል።

      • ይህም ልጅ የጳውሎስ የእህቱ ልጅ ነበር።

      • ልጁም ጳውሎስን ይጠብቀው ወደነበረው የሮም መቶ አለቃ ደፍሮ ሄደና ተናገረ።

      • መቶ አለቃውም ልጁ የነገረውን ከቁም ነገር ወስዶ ወደ ጦር አዛዡ ወሰደው።

      • የጦር አዛዡም አምኖት ጳውሎስን ለመጠበቅ “ሁለት መቶ ወታደሮችን፣ ሰባ ፈረሰኞችን እና ሁለት መቶ ጦረኞችን” አዘጋጀ።

    እነዚህ እያንዳንዳቸው ክስተቶች የመፈጠር እድላቸው እጅግ በጣም አናሳ ነበር። ነገር ግን አስደናቂው ነገር፣ ሁሉም ክስተቶች ተገጣጥመውና ተከታትለው ተፈጠሩ።

    እነዚያ ተርበው ጥቃት ለማድረስ የመሸጉት ሰዎች ያላስተዋሉት አንድ ነገር ነበር። ከእነርሱ ሴራ በፊት በጳውሎስ በኩል የተፈጠረውን አልተረዱም። ጌታ በእስር ቤት ውስጥ ለጳውሎስ ተገልጦ እንዲህ ብሎት ነበር፦ “ጳውሎስ ሆይ አይዞህ! በኢየሩሳሌም እንደ መሰከርክልኝ፣ በሮምም ደግሞ ልትመሰክርልኝ ይገባሃል” (ሐዋሪያት 23፥11)።

    ጳውሎስ ወደ ሮም ይሄዳል ብሎ ክርስቶስ ተናግሯል። ይኸው ነው። የትኛውም ዓይነት ጥቃት ክርስቶስ የሰጠውን የተስፋ ቃል ሊያስቆም አይችልም። ሮም እስከሚደርስ ድረስ ጳውሎስ የማይሞት ነበር። በዚያ ለመጨረሻ ጊዜ የሚሰጠው ምስክርነት ነበር። ክርስቶስ ደግሞ ጳውሎስ ይህን ምስክርነቱን እንዲሰጥ ያደርጋል።

    እናንተም የምትሰጡት የመጨረሻ ምስክርነት አላችሁ። ያንንም እስከምትሰጡ ድረስ በምንም ተዓምር አትሞቱም።