ምቾታችን ከየት የሚመጣ ነው? | መጋቢት 1

ወደ ግቢው ተመልሶ ኢየሱስን፣ “ከየት ነው የመጣኸው?” በማለት ጠየቀው፤ ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰለትም። ጲላጦስም፣ “አታናግረኝምን? ልፈታህ ወይም ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅም?” አለው። ኢየሱስም፣ “ከላይ ባይሰጥህ ኖሮ በእኔ ላይ ሥልጣን ባልኖረህ ነበር፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ሰው የባሰ ኀጢአት አለበት” አለው። (ዮሐንስ 19፥9-11)

ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ጲላጦስ ሊሰቅለው እንደሚችል ቢያውቅም አልተሸበረም። ለምን?

ጲላጦስ ውሸታም ስለሆነ አይደለም፤ ሥልጣኑም ስለሌለውም አይደለም።

ነገር ግን ኢየሱስ ያልፈራው የጲላጦስ ሥልጣን ከላይ ከአብ የተሰጠው ስለነበር ነው። ይህም ማለት የእውነትም ሥልጣኑ ነበረው ማለት ነው። ያነሰ ሳይሆን የበለጠ ሥልጣን ነበረው።

ታዲያ ይሄ እንዴት አያስደነግጥም? ጲላጦስ ኢየሱስን ለመግደል ከእግዚአብሔር የተሰጠ ሥልጣን ነበረው።

ኢየሱስ ያልተሸበረው ጲላጦስ በእርሱ ላይ ያለው ሥልጣን፣ እግዚአብሔር በጲላጦስ ላይ ላለው ሥልጣን ተገዢ እንደሆነ ስለሚያውቅ ነው። ኢየሱስ በዚያ ሰዓት ምቾት የሚሰማው የጲላጦስ ፈቃድ አቅም ስለሌለው ሳይሆን፣ የተመራ ስለሆነ ነው። ኢየሱስ በጲላጦስ እጅ ሳይሆን፣ ጲላጦስ በአባቱ እጅ ስለነበር ነው።

ይህም ማለት ምቾታችን የሚመጣው ከጠላቶቻችን አቅም ማጣት የተነሣ ሳይሆን፣ አባታችን በእነርሱ ላይ ካለው ሉዓላዊ ሥልጣን የተነሳ ነው።

ሮሜ 8፥35-37 ዋና ሐሳብ ይህ ነው፦ መከራ፣ ጭንቀት፣ ስደት፣ ራብ፣ ራቁትነት፣ ፍርሀት፣ ወይም ሰይፍ ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን አይችልም። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።

የኢየሱስና የእኛም ጠላቶች፣ ጲላጦስም ለክፉ ነበር ያሰቡት። እግዚአብሔር ግን ለበጎ አዋለው (ዘፍጥረት 50፥20)። የኢየሱስ ጠላቶች እግዚአብሔር በሰጣቸው ሥልጣን እጁና አሳቡ እንዲሆን አስቀድመው የወሰኑትን ሁሉ ሊፈጽሙ በዚች ከተማ በእውነት ተሰበሰቡ (ሐዋርያት 4፥28)። የኢየሱስ ጠላቶች ኅጢአትን ሠሩ፤ በእነርሱ ኅጢአት ግን እግዚአብሔር ዓለምን አዳነ።

ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ (ማቴዎስ 10፥28)። ማድረግ የሚችሉት ይህን ብቻ ነው (ሉቃስ 12፥4)። ይህንንም ሲያደርጉ በአባታችሁ ቁጥጥር ሥር ብቻ ሆነው ነው።

አምስት ድንቢጦች በዐሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ይሁን እንጂ ከእነርሱ አንዷ እንኳ በእግዚአብሔር ዘንድ አትዘነጋም። የእናንተ የራሳችሁ ጠጕር ሁሉ እንኳ የተቈጠረ ነው፤ እንግዲህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች የበለጠ ዋጋ አላችሁ። (ሉቃስ 12፥6-7)

ጲላጦስ ሥልጣን ነበረው። ሄሮድስ ሥልጣን ነበረው። ወታደሮች ሥልጣን አላቸው። ሰይጣን ሥልጣን አለው። ሁሉም ግን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ተገዢ ናቸው። አትፍሩ፤ ለሉዓላዊው አባታችሁ ውድ ናችሁ። ካልተረሱት ወፎች የበለጠ ውድ ናችሁ።