የአብርሃም ልጆች እነማን ናቸው? | ሰኔ 4

“በምድር የሚኖሩ ሕዝቦች፣ በአንተ አማካይነት ይባረካሉ።” (ዘፍጥረት 12፥3)

እናንተ በክርስቶስ ተስፋ የምታደርጉና በእምነት በመታዘዝ የምትከተሉት ሁላችሁ፣ የአብርሃም ዘሮች እና የቃል ኪዳኑ ወራሾች ናችሁ። 

እግዚአብሔር በዘፍጥረት 17፥4 ላይ፣ አብርሃምን እንዲህ ይለዋል፦ “እነሆ፤ የምገባልህ ኪዳን ይህ ነው፤ የብዙ ሕዝቦች አባት ትሆናለህ።” ነገር ግን፣ የዘፍጥረት መጽሐፍ አብርሃም ሥጋዊም ሆነ ፖለቲካዊ በሆነ መልኩ፣ የብዙ አሕዛብ አባት እንዳልነበረ በግልጽ ይነግረናል። ስለዚህ፣ የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ትርጉም፣ “ምንም እንኳን ከአብርሃም ጋር በሥጋ ባይገናኙም፣ ብዙ አሕዛብ ግን በሆነ መንገድ የልጅነት በረከቶችን ያገኛሉ” የሚል ነበር ማለት ነው።

እግዚአብሔር በዘፍጥረት 12፥3 ላይ ለአብርሃም፣ “በምድር የሚኖሩ ሕዝቦች፣ በአንተ አማካይነት ይባረካሉ” ሲለው ምን ማለቱ እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም። እግዚአብሔር ገና ከጀማሬው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብርሃም ዘር እንደሚሆንና በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ ደግሞ የአብርሃም የተስፋ ቃል ወራሾች እንደሚሆኑ አስቦ ነበር። ጳውሎስ በገላትያ 3፥29 ላይ፣ “የክርስቶስ ከሆናችሁ፣ እናንተ የአብርሃም ዘር ናችሁ፤ እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ” በማለት ይናገራል።

ስለዚህ፣ ከ4,000 ዓመታት በፊት፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም፦ “እነሆ፤ የምገባልህ ኪዳን ይህ ነው፤ የብዙ ሕዝቦች አባት ትሆናለህ” ሲለው፣ ከየትኛውም ዘር ሆንን ከየትኛውም ነገድ፣ ለእያንዳንዳችን፣ የአብርሃም ልጅ እና የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ወራሽ እንሆን ዘንድ መንገዱን ከፍቶልናል ማለት ነው። ማድረግ የሚጠበቅብን አንድ ነገር፣ የአብርሃምን እምነት መካፈል ብቻ ነው። ይህም ማለት፣ ተስፋችንን በእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች ላይ ማድረግ፤ እንዲሁም፣ መታዘዝ የሚያስፈልግ ከሆነም፣ አብርሃም ይስሐቅን አሳልፎ እንደሰጠው፣ በጣም የምንወደውን ንብረታችንን እንኳን አሳልፈን እስክንሰጥ ድረስ በእግዚአብሔር መታመን ማለት ነው። 

እግዚአብሔር ለእኛ እንደሚሠራ በመተማመን እንጂ፣ ለእግዚአብሔር በመስራት የአብርሃም የተስፋ ቃል ወራሾች አንሆንም። “ይልቁንም [አብርሃም] በእምነቱ በመጽናት ለእግዚአብሔር ክብርን ሰጠ እንጂ፣ የእግዚአብሔርን ተስፋ አልተጠራጠረም፤ እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም በሙሉ ልብ ርግጠኛ ነበር” (ሮሜ 4፥20–21)። ለዚህም ነው አብርሃም መታዘዝ የሞት ጎዳና በመሰለበት ሁኔታ እንኳ እግዚአብሔርን መታዘዝ የቻለው። ልጁን ከሞት እስከማስነሳት ድረስ የማይቻለውን እንደሚያደርግ እግዚአብሔርን አመነ። 

በእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች ማመን — ወይም ዛሬ ላይ እንደምንለው፣ የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ማረጋገጫ በሆነው፣ በክርስቶስ ማመን — የአብርሃም ልጅ የምንሆንበት መንገድ ነው። መታዘዝ ደግሞ የእምነታችንን እውነተኛነት የምናረጋግጥበት መንገድ ነው (ዘፍጥረት 22፥12-19)። ስለዚህም፣ ኢየሱስ በዮሐንስ 8፥39 ላይ፣ “የአብርሃም ልጆችስ ብትሆኑ፣ አብርሃም የሠራውን ትሠሩ ነበር” ይሏል። 

የአብርሃም ልጆች ተስፋቸውን በክርስቶስ ላይ ያደረጉ፣ ከሁሉም ህዝብ የተውጣጡ ሰዎች ናቸው። እናም፣ አብርሃም በሞሪያ ተራራ ላይ እንዳደረገው፣ እጅግ ውድ የሚሉትን ምድራዊ ሃብታቸውን ማጣት፣ ከመታዘዝ እንዲያስቆማቸው አይፈቅዱለትም።

እናንተ በክርስቶስ ተስፋ የምታደርጉና በእምነት በመታዘዝ የምትከተሉት ሁላችሁ፣ የአብርሃም ዘሮች እና የቃል ኪዳኑ ወራሾች ናችሁ።