ኢየሱስን ማን ገደለው? | ሚያዚያ 25

ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም? (ሮሜ 8፥32)

ከበርካታ ዓመታት በፊት፣ በአሜርካ ግዛት ውስጥ ባለች ኢሊኖይስ በምትባል ከተማ መጋቢ ሆኖ ያገለግል የነበረ አንድ ጓደኛዬ፣ በሆሳእና በዓል ሳምንት፣ በመንግስት እስር ቤት ውስጥ ለታሰሩ እስረኞች ይሰብክ ነበር። በመልዕክቱም መሀል ቆም በማለት እስረኞቹን፣ ኢየሱስን የገደለው ማን እንደሆነ ያውቁ እንደሆነ ይጠይቃቸዋል።

ታዲያ አንዳንዶቹ ወታደሮቹ ናቸው ሲሉ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ አይሁዶች ናቸው አሉ። ሌሎቹም ጲላጦስ በማለት መለሱ። ከዚያም ጓደኛዬ ዝም እስኪሉ ጠበቀና “አባቱ ነው የገደለው” ብሎ መለሰላቸው።  

ሮሜ 8፥32 የመጀመሪያ አጋማሽ የሚለው ይህንን ነው፦ እግዚአብሔር ለገዛ ልጁ አልራራለትም፤ ነገር ግን ለሞት አሳልፎ ሰጠው። “እግዚአብሔር በጥንት ውሳኔውና በቀደመው ዕውቀቱ ይህን ሰው [ኢየሱስን] አሳልፎ በእጃችሁ ሰጣችሁ” (ሐዋርያት ሥራ 2፥23)። ኢሳይያስ 53ም የበለጠ ግልጽ በሆነ መንገድ ያስቀምጠዋል፦ “እኛ ግን በእግዚአብሔርም እንደ ተመታ፣ እንደ ተቀሠፈ እንደ ተሠቃየም ቈጠርነው። . . . መድቀቁና መሠቃየቱ ግን የእግዚአብሔር (የአባቱ) ፈቃድ ነበር” (ኢሳይያስ 53፥​4, 10)።

ወይም ደግሞ ሮሜ 3፥25 እንደሚናገረው፣ “እግዚአብሔር የማስተስረያ መሥዋዕት አድርጎ [እርሱን] አቅርቦታል።” ልክ አብርሃም በልጁ በይስሐቅ አንገት ላይ ቢላውን እንዳነሣ፣ ነገር ግን በዱር ውስጥ በግ ስለ ነበረ ልጁን እንዳተረፈው ሁሉ፣ እግዚአብሔር አብም በልጁ በኢየሱስ አንገት ላይ ቢላዋውን አነሣ — ነገር ግን አልራራለትም፤ ምክንያቱም ያ በግ እርሱ ነበር፤ እርሱ ምትካችን ነበር።

እግዚአብሔር ለገዛ ልጁ አልራራለትም፤ ምክንያቱም ጻድቅ እና ቅዱስ አምላክ መሆኑ ሳይነካ፣ ለእኛ ርህራሄን ሊያሳየን የሚችልበት ብቸኛው መንገድ ይህ ነበር። የመተላለፋችን ጥፋት፣ ለበደላችን የሚገባን ቅጣት እና የኃጢአታችን እርግማን ወደማናመልጥበት የገሃነም ጥፋት ይከተን ነበር። እግዚአብሔር ግን ለገዛ ልጁ አልራራለትም፤ ስለ መተላለፋችን እንዲወጋ፣ ስለ በደላችንም እንዲደቅቅ፣ ስለ ኃጢአታችንም እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው።  

ይህ ክፍል — ሮሜ 8፥32 — እጅግ አብልጬ የምወደው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው። ሁሉን አቀፍ ለሆነው የእግዚአብሔር የወደፊት የጸጋ ተስፋ መሠረት የሚሆን ክፍል ነው። ታላቅና ቅዱስ በሆነ አምላክ ፊት ይቅር ተብዬ፣ ከእርሱም ጋር ታርቄ፣ ጸድቄ፣ ተቀባይነት አግኝቼ፣ በቀኙም ከዘላለም እስከ ዘላለም የማይነገሩት የተድላ ተስፋዎች ተካፋይ ሆኜ እቆም ዘንድ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ቅጣቴን፣ በደሌን፣ ኩነኔዬን፣ መተላለፌን ሁሉ በስጋው ተሸከመ። ክብር ለዘለዓለም ለስሙ ይሁን!