ኢየሱስ የመጣበት ምክንያት | ታሕሳስ 15

ልጆቹ በሥጋና በደም እንደሚካፈሉ እርሱ ራሱ ደግሞ ያንኑ ተካፈለ፤ ይኸውም በሞት ላይ ኀይል ያለውን ዲያቢሎስን በሞቱ ኀይል እንዲደመስስ ነው፤ እንዲሁም በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በሞት ፍርሀት ባርነት የታሰሩትን ነጻ እንዲያወጣ ነው።

ዕብራውያን 2፥14-15 (አ.መ.ት)

ስለ ኢየሱስ መወለድ ከሚናገሩ ጥቅሶች መካከል፣ ዕብራውያን 2፥14-15ን ከሁሉም ይልቅ እወደዋለሁ ብዬ አስባለሁ። ምክንያቴ ደግሞ እንደዚህ ጥቅስ የኢየሱስን ምድራዊ ሕይወት አጀማመር እና አጨራረስ፣ ተሰግኦውን እና ስቅለቱን በአንድ ላይ አያይዞ የሚገልጽ ሌላ ጥቅስ ስለማላውቅ ነው። ኢየሱስ የመጣበት ዋነኛ ምክንያት ለመሞት እንደሆነ ከእነዚህ ሁለት ቁጥሮች በግልጽ እንረዳለን። አማኝ ላልሆኑ ጓደኞቻችን ወይም ቤተሰቦቻችን የገናን በዓል ምንነት በሒደት ለማስረዳት በጣም የሚጠቅም ጥቅስ ነው። ሐረጎቹን አንድ በአንድ እየነጠልን በዚህ መልኩ ልናብራራው እንችላለን፤

…ልጆቹ በሥጋና በደም እንደሚካፈሉ…

ልጆቹ” የሚለው ቃል የተወሰደው ቀደም ብሎ ካለው ቁጥር (ዕብራውያን 2፥13) ሲሆን የሚወክለውም የመሲሑን መንፈሳዊ ልጆች ነው (ኢሳይያስ 8፥1853፥10ን ይመልከቱ)። የእግዚአብሔር ልጆችም ናቸው (ዮሐንስ 1፥12)። በሌላ አገላለጽ፣ እግዚአብሔር የልጆቹን መዳን ታሳቢ አድርጎ ነው ክርስቶስን የላከው ማለት ነው።

እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ዓለሙን እንዲሁ ወድዷልና” (ዮሐንስ 3፥16) የሚለው እውነት እንደሆነ እናውቃለን። ግን ደግሞ ሌላው እውነታ እግዚአብሔር፣ “የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች በአንድነት” ልዩ በሆነ መንገድ ለመሰብሰብ እንደነበር እናውቃለን (ዮሐንስ 11፥52)። የእግዚአብሔር ዕቅድ ክርስቶስን ለዓለም ሊያቀርብ እና ለልጆቹ ደግሞ መዳናቸውን ሊፈጽም ነው (1ኛ ጢሞቴዎስ 4፥10)። ክርስቶስን በመቀበል የማደጎ ልጆች ልትሆኑ ትችላላችሁ (ዮሐንስ 1፥12)።

… እርሱ ራሱ ደግሞ ያንኑ [ሥጋና ደምን] ተካፈለ …

ይህ ማለት ክርስቶስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሕልውና ነበር ማለት ነው። ከእግዚአብሔር ጋር ነበር፤ እግዚአብሔር ነበር (ዮሐንስ 1፥1ቆላስያስ 2፥9)። ነገር ግን ሥጋና ደምን ተካፈለ፣ አምላክነቱንም ላይ ሰውነትን ለበሰ። ፍጹም አምላክነቱን ሳይለቅ ፍጹም ሰው ሆነ። ከብዙ ነገር አንጻር ይህ አስደናቂ ሚስጥር ነው። ሆኖም ግን የእምነታችን ማዕከል እና የመጽሐፍ ቅዱስም አሰተምህሮ ነው።

… በሞቱ …

ይህ ነው የመጣበት ዓላማ። ለመሞት። በግልጽ የምናውቀው ነገር እንደ አምላክ ለኀጢአተኞች ሊሞት አይችልም። ነገር ግን እንደ ሰው ይችላል። ግቡ መሞት ነበር። ስለዚህም፤ ሰው ሆኖ መወለድ ነበረበት። የተወለደው ለመሞት ነበር። የገና በዓል ዋና ዓላማው የስቅለት በዓል ነበር። ብዙዎች ስለ ገና ትርጉም ዛሬ ሊሰሙት የሚገባው ሐቅ ይህ ነው።

… ይኸውም በሞት ላይ ኀይል ያለውን ዲያቢሎስን በሞቱ ኀይል እንዲደመስስ ነው …

ክርስቶስ በሞቱ የዲያቢሎስን ኀይል አድቅቋል። እንዴት? ኀጢአታችንን ሁሉ በመሸፈን። ይህ ማለት ሰይጣን እኛን በእግዚአብሔር ፊት ለመክሰስ አንዳች መሠረት የለውም ማለት ነው። “እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኰንንስ ማን ነው?” (ሮሜ 8፥33)። በምን መሠረት ነው የሚያጸድቀው? በክርስቶስ ደም ላይ (ሮሜ 5፥9)።

ሰይጣን በእኛ ላይ ሊጠቀመው የሚችለው ከፍተኛው መሳሪያ የራሳችንን ኀጢአት ነው። ኀጢአታችንን ደግሞ የኢየሱስ ሞት የሚሽርልን ከሆነ፣ ሰይጣን ያለው ዋነኛ መግደያ መሣሪያ ከእጁ ተነጥቋል ማለት ነው። ዳኛው በልጁ ሞት ምክንያት “ነጻ ናችሁ!” ብሎ ክሱን ስለዘጋው ከሳሻችን እኛ ላይ ሞት ለማስፈረድ አንድም ክስ ሊያቀርብ አይችልም።

… እንዲሁም በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በሞት ፍርሀት ባርነት የታሰሩትን ነጻ እንዲያወጣ ነው።

ስለዚህ ከሞት ፍርሀት ነጻ ወጥተናል ማለት ነው። እግዚአብሔር አጽድቆናል። ሰይጣን ይህንን ውሳኔ ሊያስቀለብስ ፈጽሞ አይችልም። ዘላቂውና የመጨረሻው ደህንነታችን ደግሞ አሁን ላይ ላለው ሕይወታችን አፋጣኝ የሆነ ውጤት እንዲኖረው እግዚአብሔር ይፈልጋል። አሁን ላይ የተጋረጠብንን ባርነት እና የሞት ፍርሀት አስደሳቹ ፍጻሜ እንዲያስወግድልን ይሻል።

የመጨረሻው እና ዋነኛውን ጠላታችንን ሞትን የምንፈራው ካልሆነ፣ አንዳች የምንፈራው ነገር ሊኖር አይችልም ማለት ነው። ነጻ መሆን እንችላለን። ለደስታና ለሐሴት ነጻ፣ ሌሎችን ለመውደድና ለማገልገል ነጻ ልንሆን እንችላለን።

እግዚአብሔር የሰጠን የገና ስጦታ ምንኛ ታላቅ ነው!? እኛ ደግሞ ይህንን ስጦታ ለዓለም ሁሉ እንሰጣለን!