“ስለዚህ ተስፋ አንቈርጥም፤ ውጫዊው ሰውነታችን እየጠፋ ቢሄድም እንኳ፣ ውስጣዊው ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል፤ ምክንያቱም ቀላልና ጊዜያዊ የሆነው መከራችን ወደር የማይገኝለት ዘላለማዊ ክብር ያስገኝልናል። ስለዚህ ዐይናችን የሚያተኵረው በሚታየው ነገር ላይ ሳይሆን በማይታየው ላይ ነው፤ የሚታየው ጊዜያዊ ነውና፤ የማይታየው ግን ዘላለማዊ ነው” (2ኛ ቆሮንቶስ 4፥16-18)።
ጳውሎስ እንደ ቀድሞው ማየት አይችልም። በጊዜው ደግሞ መነጽር የሚባል ነገር አልነበረም። እንደ ቀድሞውም መስማት አይችልም። በጊዜው ምንም ማድመጫ መሳሪያዎች አልነበሩም። እንደ ወጣትነቱም ከድብደባ ጉዳት ፈጥኖ አያገግምም። በጊዜው ደግሞ ጸረ-ባክቴሪያ መድኀኒቶች አልነበሩም። ከከተማ ወደ ከተማ በእግር የመሄድ ጥንካሬው እንደ ቀድሞው አይደለም። ፊቱ እና አንገቱ በእርጅና ተሸብሽቧል፣ የማስታወስ ክህሎቱም ምናልባት ተዳክሟል። ደግሞም ይህ ለእምነቱ፣ ለደስታው እና ለድፍረቱ ተግዳሮት እንደሆነ ተቀብሏል።
ነገር ግን ተስፋ አይቆርጥም፤ ለምን?
የውስጥ ሰውነቱ እየታደሰ ስለሆነ ተስፋ አይቆርጥም። ቆይ ግን እንዴት?
የልቡ መታደስ የሚመጣው ካልተለመደ ስፍራ ነው። ሊያየው የማይችለውን ነገር በመመልከት እንደ አዲስ ያንሰራራል።
ስለዚህ ዐይናችን የሚያተኩረው በሚታየው ነገር ላይ ሳይሆን በማይታየው ላይ ነው፤ የሚታየው ጊዜያዊ ነውና የማይታየው ግን ዘላለማዊ ነው።
(2ኛ ቆሮንቶስ 4፥18)
ጳውሎስ ራሱን ተስፋ ከመቁረጥ የሚታደገው የማይታየውን ነገር በመመልከት ነው። ታዲያ ሲመለከት ምን አየ?
ከጥቂት ቁጥሮች በኋላ በ2ኛ ቆሮንቶስ 5፥7 ላይ፣ “በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስም” ይላል። ይህ ማለት ግን ወደ ባዶ ጭለማ ምን እንዳለ ሳያረጋግጥ በጭፍን ዘው ብሎ ይገባል ማለት አይደለም። ይልቁንም በአሁኑ ጊዜ፣ በዚህ ዓለም ከሚገኝ ከምንም ነገር እጅ የሚልቁና ውድ የሆኑ ወሳኝ እውነታዎች ከሥጋዊ ስሜታችን በላይ ናቸው ማለት ነው።
እነዚህን የማይታዩ ነገሮች በወንጌል አማካይነት “እናያቸዋለን”። ክርስቶስን ፊት ለፊት ባዩ ሰዎች ምስክርነት ላይ ተመስርተን፣ ዓይናችንን በማይታየው ነገር ላይ በመትከል ልባችንን እናጠነክራለን፣ ድፍረታችንንም እናድሳለን።
“በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን ይሰጠን ዘንድ፣ ‘በጨለማ ብርሃን ይብራ’ ያለው እግዚአብሔር ብርሃኑን በልባችን አብርቷልና” (2ኛ ቆሮንቶስ 4፥6)። “በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔር የክብሩን እውቀት ብርሃን” በወንጌሉ አማካኝነት በልባችን ሲያበራ እናያለን።
ተረዳነውም አልተረዳነውም እኛ ክርስቲያኖች የሆንነው ይህ ሲከሰት ነው። ስለዚህ ተስፋ እንዳንቆርጥ ከጳውሎስ ጋር በልባችን ዓይኖች አተኩረን ልንመለከት ይገባናል።