ተስፋችንን አጥብቀን ምንይዝበት ምክንያት | መጋቢት 18

“እግዚአብሔር የማይለወጥ ዐላማውን ለተስፋው ቃል ወራሾች ግልጽ ለማድረግ ስለ ፈለገ፣ በመሐላ አጸናው፤ እግዚአብሔር ከቶ ሊዋሽ አይችልም፤ እርሱ በሁለት በማይለወጡ ነገሮች በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ወደ እርሱ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት እንድናገኝ አድርጎአል (ዕብራውያን 6፥17-19)

እግዚአብሔር አይለዋወጥም። በተስፋ ቃሎች፣ በቃል ኪዳኖች እና በልጁ ደም ራሱን በማስገደድ፣ አንዱን የደኅንነታችንን ክፍል ለመጠበቅ ሲል ሌላኛውን የሚተው አምላክ አይደለም።

በኢየሱስ በደም የተገዛው ደኅንነት፣ ሕዝቦቹን ከሁሉም ነገሮች ለማዳን የፈሰሰ እንጂ ለአንዳንድ ነገሮች ብቻ የፈሰሰ አይደለም።

ታዲያ ጸሐፊው ተስፋችንን አጥብቀን እንድንይዝ ለምን ይጠይቀናል (ዕብራውያን 6፥18)? የተስፋ ቃሎቻችን በኢየሱስ ደም ላይቀየሩ የተረጋገጡ ናቸው። በአዲስ እና በብሉይ ኪዳን መካከል ያለው ልዩነት ይህ ነው። ታዲያ ለምንድን ነው እግዚአብሔር በተረጋገጠ ነገር ላይ እነዚህን የተስፋ ቃሎች አጥብቀን እንድንይዝ የሚነግረን?

መልሱ ይህ ነው፦

  • ኢየሱስ በሞቱ የገዛልን፣ አጥብቆ ከመያዝ ኅላፊነት ነፃ የሚያደርገንን ሳይሆን፣ እንዲያውም ተስፋችንን አጥብቀን ለመያዝ የምንችልበትን ኅይል ነው።
  • በደሙ የገዛው የፈቃዳችንን መወገድ ሳይሆን፣ በፈቃዳችን ተስፋችንን አጥብቀን እንድንይዝ የምንችልበትን ኅይል ነው።
  • በደሙ ተስፋን አጥብቆ የመያዝ ትዕዛዝን አልሻረውም፤ ይልቅ እንዲጸና አደረገው።
  • በደሙ ማበረታቻዎች እንዲወገዱ አላደረገም፤ ይልቅ ማበረታቻ አሸንፎ እንዲወጣ አደረገ።

ኢየሱስ የሞተው ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 3፥12 ያደረገውን እንድታደርጉ ነው፦ “ክርስቶስ ኢየሱስ እኔን የራሱ ያደረገበትን ያን፣ እኔም የራሴ ለማድረግ እጣጣራለሁ።” አንድ ኅጢአተኛ፣ ኢየሱስ ብቻ በሚሰጠው አቅም በእግዚአብሔር ተስፋ እንዲያደርግ መናገር ሞኝነት አይደለም። ስለዚህ ከልቤ አሳስባችኋለሁ፣ እጃችሁን ዘርጉና በክርስቶስ የተያዛችሁበትን በኅይል የሚሠራባችሁን የተስፋ ቃል በሙሉ አቅማችሁ አጥብቃችሁ ያዙ።