ጠላቶቻችንን ለምን እንውደድ? | ግንቦት 13

“ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ።” (ሉቃስ 6፥27)

ክርስቲያኖች ጠላቶቻቸውን ሊውድዱና ለሚጠሏቸውም መልካምን ሊያደርጉ የሚገባባቸው ሁለት ምክንያቶች አሉ።

የመጀመሪያው፣ ይህን ማድረግ የእግዚአብሔርን አንድ ባሕሪ የሚገልጥ መሆኑ ነው። እግዚአብሔር መሐሪ ነው።

  • እርሱ ፀሓዩን ለክፉዎችና ለደጎች ያወጣል፤ ዝናቡንም ለኀጢአተኞችና ለጻድቃን ያዘንባል። (ማቴዎስ 5፥45)
  • እንደ ኀጢአታችን አልመለሰልንም፤ እንደ በደላችንም አልከፈለንም። (መዝሙር 103፥10)
  • እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ፣ እናንተም ይቅር ተባባሉ፤ እርስ በርሳችሁ ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ (ኤፌሶን 4፥32)።

ስለዚህ፣ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ኅይል በመረዳት በዚህ መንገድ ስንኖር፣ እግዚአብሔር ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ማሳየት እንችላለን።

ሁለተኛው ምክንያት፣ የክርስቲያኖችን ልብ በበቀል ስሜት፣ በገንዘብ ወይም በግላዊ ደህንነት የሚመራ አለመሆኑና፣ የሚረካው በእግዚአብሔር ብቻ መሆኑ ነው።

እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ የሚያረካ ውድ ሀብት ሆኖልናል። ስለዚህም ጠላቶቻችንን ከፍርሃት ተነስተን አናጠቃቸውም፣ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ክብር እንደጠገበ ሰው ምላሽ እንሰጣለን።

“እናንተ ራሳችሁ የተሻለና ለዘወትር የሚኖር ሀብት ያላችሁ መሆናችሁን ስለምታውቁ ለታሰሩት ራራችሁ፤ ንብረታችሁም ሲዘረፍ በደስታ ተቀበላችሁ [ይህ ማለት፣ ጠላቶቻችሁን አልተበቀላቸሁም ማለት ነው]” (ዕብራውያን 10፥34)። የበቀል ስሜትን ሊያጠፋ የሚችለው ብቸኛ ነገር፣ ይህ ዓለም ዘላቂ ቤታችን አለመሆኑን ማወቃችንና ከምንም ነገር በላይ በሙላት በሚያረካን በእግዚአብሔር ከልብ መታመናችን ነው። “የተሻለና ለዘወትር የሚኖር ሀብት” እንደሚጠብቀን እናውቃለን።

ስለዚህ፣ በእነዚህ ሁለት ጠላቶቻችንን የመውደድ ምክንያቶች ውስጥ የሚታየው ዋና ነገር፦ (1) እግዚአብሔር መሐሪ መሆኑ እና (2) በሙላቱ ክብር ሁሉን የሚያረካ መሆኑ ነው።

ምህረት ለማድረግ ኃይል የሚኖረን፣ እኛ ራሳችን ከእግዚአብሔር ምህረት የጠገብን እንደሆነ ነው። ደግሞም ምህረት የምናደርግበት ዋነኛ ምክንያት፣ እግዚአብሔር ይከብር ዘንድ እና ሌሎችም እግዚአብሔርን ለምህረቱ ያመሰግኑት ዘንድ ነው። እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ መሆኑን ማሳየት ይገባናል። በሰው ሁሉ ዓይን ፊት እግዚአብሔር በፍቅራችን ምክንያት ልቆ፣ በልጦ፣ እና ገናና ሆኖ እንዲታይ ልንጓጓ ይገባል።