ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ፤ ያደቀቅሃቸው ዐጥንቶቼም ደስ ይበላቸው። … የማዳንህን ደስታ መልስልኝ፤ በእሽታ መንፈስም ደግፈህ ያዘኝ (መዝሙር 51፥8፣ 12)።
የዳዊት ልመና እዚህ ጋር ምንድን ነው? ለምንድን ነው ወሲባዊ ስሜቶቹ እንዲታሰሩ ያልጸለየው? ወይም ደግሞ ለምንድን ነው በዙሪያው ያሉ ሰዎች በኀላፊነት እንዲከታተሉት ያልጸለየው? ለምንድስ ነው ዓይኖቹ እና አዕምሮው ከወሲባዊ ኅጢአት እንዲጠበቁለት ያልጸለየው? ይህንን የኑዛዜ እና ንሰሓ መዝሙር ዳዊት የጸለየው ቤርሳቤህ ላይ ከመድፈር ያልተናነሰ ጥቃት ካደረሰባት በኋላ ስለሆነ፣ እንዲህ ዐይነት ጸሎት ይጸልያል ተብሎ ይጠበቃል።
ምናልባትም እንዲህ ያልጸለየበት ምክንያቱ ወሲባዊ ኀጢአት በሽታው ሳይሆን ምልክቱ እንደሆነ ስለሚያውቅ ነው።
ሰዎች ለወሲባዊ ኀጢአት በሮችን የሚከፍቱበት ዋነኛው ምክንያት፣ በክርስቶስ የሚገኝ ሙሉ የሆነ ደስታና ሐሴት ስለሌላቸው ነው። መንፈሳቸው የጸና፣ የረካና የተደላደለ አይደለም። ይዋልላሉ። ስሜታቸው ስላልተገዛ፣ በቀላሉ ይታለላሉ። እግዚአብሔር በሐሳባቸው ውስጥ የሚገባውን ቀዳሚ ስፍራ ስላልያዘ ለአፍታ ለሚቆይ የኀጢአት ደስታ በራቸውን ክፍት ያደርጋሉ።
ዳዊት ይህንን ስለራሱ ያውቅ ነበር። የእኛም ጉዳይ እንዲሁ ተመሳሳይ ነው። ዳዊት በጸሎቱ ይህንን ያሳየናል፤ በወሲባዊ ኀጢአት ለሚወድቁ በእውነት የሚያስፈልጋቸው አንድ እና አንድ ነገር ብቻ ነው፤ እርሱም እግዚአብሔር እና በእርሱ ውስጥ ያለው ደስታ ነው።
ይህ ለእኛ ጥልቅ የሆነ ጥበብ ነው።