አካል የተሰጣችሁ በምክንያት ነው | ነሐሴ 3

በዋጋ ተገዝታችኋልና፤ ስለዚህ በሰውነታችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ (1ኛ ቆሮንቶስ 6፥20)።

እግዚአብሔር አካላዊና ቁሳዊውን ዓለም የፈጠረው እንዲያው ዝም ብሎ አይደለም። አላማ ነበረው፤ ይኸውም ክብሩ የበለጠ የሚታይበትና የሚገለጥበት መንገዶችን ለመጨመር ነው። “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያውጃሉ” (መዝሙር 19፥1)።

ሰውነታችንም እግዚአብሔር በዚህ ምክንያት ከፈጠራቸው አካላዊ ነገሮች ምድብ ውስጥ ይካተታል። እግዚአብሔር በሰዎች አካልና ሁለንተና ውስጥ ራሱን ለማክበር ካለው እቅድ ወደ ኋላ አይልም።

ታዲያ እግዚአብሔር ይህን የሚበሰብስ በኃጢአት የተበከለ ሥጋ ለማደስ እና የዘላለማዊነትን ክብር ለማልበስ ለምንድነው የሚለፋው? መልሱም፦ ከዘላለም እስከ ዘላለም እንዲከብርበት ሲል ነው የሚል ነው። ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ የሞት ዋጋን የከፈለው ሰውነታችንን ጨምሮ አብ ለቁሳዊው ዓለም ያለው ዓላማ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ነው።

ክፍሉም ለዚህ ነው “በዋጋ ተገዝታችኋልና፤ ስለዚህ በሰውነታችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ” የሚለው። ዋጋውም የልጁ መሞት ነው። እግዚአብሔር የልጁን ሥራ ሳያከብር ችላ ብሎ አይተወውም። እግዚአብሔር የልጁን ሥራ እኛን ከሞት በማስነሣት ያከብራል፤ እኛም ደግሞ ሰውነታችንን እርሱን ለማክበር ለዘላለም እንጠቀምበታለን።

ስለዚህ አሁን ላይ አካል ያላችሁ ለዚህ ነው። ደግሞም የክርስቶስን ክቡር ሥጋ እንዲመስል ከሞት የሚነሣውም በዚህ ምክንያት ነው።