ፍርሀቶቻችሁን አስወግዱ | ሕዳር 3

ፍርሀት በሚይዘኝ ጊዜ፣ እምነቴን በአንተ ላይ አደርጋለሁ። (መዝሙረ ዳዊት 56፥3)

የጭንቀታችን ምንጭ አለማመን መሆኑን ስንረዳ፣ ጥርጣሬ ይበልጥ በውስጣችን አድሮ፣ አንዱ ምላሻችን ይህ ሊሆን ይችላል፦ “ከጭንቀት ጋር በየዕለቱ እየታገልኩ ከሆነ በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ በቂ እምነት የለኝም ማለት ነው። ታዲያ እንዲህ ከአለማመን ጋር እየታገልኩ እውነት ግን በርግጥ ድኛለሁ?” እንል ይሆናል።

የመኪና ውድድር ምሳሌ በመጠቀም ለዚህ ሥጋት ምላሽ ልስጥ። ለአንድ አፍታ የመኪና ተወዳዳሪ እንደሆናችሁ እናስብ። በውድድራችሁ ወቅት፣ ውድድሩን እንድትጨርሱ የማይፈልገው ተቀናቃኛችሁ በመስታወታችሁ ላይ ጭቃ ወረወረ እንበል። እይታችሁ ስለሚጋረድ ለጥቂት ጊዜ ብትንገዳገዱ ውድድሩን አቋርጣችሁ ትወጣላችሁ ማለት አይደለም።

ወይም ደግሞ በተሳሳተ የውድድር መስመር ላይ ናችሁ ማለትም አይደለም። ቢሆንማ ኖሮ፣ ተቀናቃኛችሁ ባላስቸገራችሁ ነበር። መስታወታችሁ እንዲጸዳ እና ወደ በፊቱ ፍጥነታችሁ እንድትመለሱ ከእናንተ የሚጠበቀው የዝናብ መጥረጊያዎቻችሁን ማንቀሳቀስ ነው።

ጭንቀት ወሮን ለእግዚአብሔር ክብር ያለን እይታ ሲንሸዋረር፣ በዚህም የተዘጋጀልንን ታላቅ ዕቅድ ማየት ሲሳነን፣ ጭራሽ እምነት የለንም ወይም ወደ መንግሥተ ሰማይ አንደርስም ማለት አይደለም። እምነታችን ላይ ውጊያ ተከፍቷል ማለት ነው።

መጀመሪያ ላይ በእግዚአብሔር ተስፋዎች ላይ ያለን እምነት ለጥቂት ጊዜ ሊንገዳገድ ይችላል። ነገር ግን በመንገዱ ላይ ጸንተን የምንቆየው እና ወደ ፍጻሜው የምንደርሰው፣ በጸጋው ላይ ተመርኩዘን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ስናድርግ ነው። በአለማመን የሚወረወርብን ጭንቀትን ለማጽዳት እና መልሰን ለመቃወም የዝናብ መጥረጊያዎቻችንን በእምነት እናንቀሳቅሳቸው።

መዝሙር 56፥3 “ፍርሀት በሚይዘኝ ጊዜ፣ እምነቴን በአንተ ላይ አደርጋለሁ” ይላል።

አስተውሉ፦ “ፍርሀት መቼም አይነካኝም” አይልም። ፍርሀት ያጠቃናል፤ ውጊያም ይከፈትብናል። መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ አማኞች ጭንቀት ከቶ አይደርስባቸውም አይልም። ይልቁንም ጭንቀት ሲወረን እንዴት እንደምንዋጋ ያስተምረናል፣ ያስታጥቀናል። የዝናብ መጥረጊያዎቻችንን እንዴት ማብራት እንደምንችል ይመክረናል።