ለነፋስ የሆኑ ቃላት | ጥር 16

“ተስፋ የሌለው ሰው ንግግር እንደ ነፋስ ነውና ቃሌን ትገሥጹ ዘንድ ታስባላችሁን?” (ኢዮብ 6፥26)

በሐዘን፣ በሕመምና ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ፣ ብዙ ጊዜ ሰዎች በሌሎች ጊዜያት የማይሏቸውን ነገሮች ይናገራሉ። እውነታን ነገ ፀሐይ ስትወጣ ከሚስሉበት በበለጠ አጨልመው ይስላሉ። ሃዘንን የሚያስተጋቡ ሙዚቃዎችን በማዜም፣ ያለው ሙዚቃ እርሱ ብቻ እንደሆነ አድርገው ይናገራሉ። የሚታያቸው ደመና ብቻ ነው፤ ሰማይ እንደሌለ ዓይነት ያወራሉ።

“እግዚአብሔር የታለ?” ወይም፦ “መቀጠል ጥቅም የለውም።” ወይም፦ “ሁሉም ነገር ግራ የሚያጋባ ነው።” ወይም፦ “ለእኔ ተስፋ የለም።” ወይም፦ “እግዚአብሔር መልካም ቢሆን ኖሮ፣ ይሄ በእኔ ላይ አይሆንም ነበር” ይላሉ።

ስለ እነዚህ ቃላት ምን እናድርግ?

ኢዮብ ልንገሥፃቸው አያስፈልገንም ይላል። እነዚህ ቃላት ነፋስ ናቸው፣ ወይም በቀጥታ “ለነፋስ” የተነገሩ ናቸው። በፍጥነት ይበናሉ። ሁኔታዎችም ሲቀየሩ፣ ተስፋ የቆረጠው ሰው ከጨለማው ይነቃና ቸኩሎ በተናገረው ነገር ይፀፀታል።

ስለዚህም፣ ጊዜና ጉልበታችንን እነዚህን ቃላት በመገሠፅ አናሳልፍ። እራሳቸው በነፋስ በነው ይጠፋሉ። በመኸር ቅጠሎችን መቁረጥ አላስፈላጊ ድካም ነው፤ በራሳቸው ጊዜ ይረግፋሉና።

እግዚአብሔርን፣ አንዳንዴም እውነትን፣ ለነፋስ ከተነገሩ ቃላት ለመከላከል አቤት እንዴት እንቸኩላለን። ማስተዋል ቢኖረን፣ ስር ባላቸው ቃላትና ለነፋስ በተነገሩ ቃላት መካከል ያለውን ልዩነት በተረዳን ነበር።

ስራቸው ከጥልቅ ስህተትና ክፋት የሆኑ ቃላት አሉ። ሁሉም የጨለሙ ቃላት ግን ከክፉ ልብ አይደሉም። አንዳንዶቹ በሕመምና፣ ተስፋ በመቁረጥ የጨለሙ ናቸው። የምንሰማው ከውስጥ፣ ከልብ ያለውን አይደለም። በእርግጥ የሚመጡት እውን ከሆነና ከጨለመ ቦታ ነው። ነገር ግን ጊዜያዊ ነው – እንደሚያልፍ በሽታ – እውን ነው፣ ያማል፣ ግን እውነተኛው ማንነት አይደለም።

ስለዚህ እናስተውል፣ በእኛ ላይ፣ ወይም በእግዚአብሔር ላይ፣ ወይም በእውነት ላይ፣ የተነገሩ ቃላት ለነፋስ የተነገሩ መሆናቸውን እንለይ – ከልብ ሳይሆን ከጊዜያዊው ሕመም የመጡ። ለነፋስ የተነገሩ ከሆኑ፣ በዝምታ ያለ ግሣፄ እንጠብቅ። የፍቅራችን ዓላማ መንፈስን ማደስ እንጂ ሕመምን መገሠጽ አይደለምና።