በማዕበል ውስጥ ያለ አምልኮ | መስከረም 11

ምክንያቱም መብረቅ በርቆ ሰማዩን ከዳር እስከ ዳር እንደሚያበራ፣ የሰው ልጅም በሚመጣበት ቀን ልክ እንደዚሁ ይሆናል። (ሉቃስ 17፥24)

በሌሊት ከቺካጎ ወደ ሚኒያፖሊስ እየበረርኩ ነበር፤ በአውሮፕላኑ ውስጥ ጥቂት ሰዎች ብቻ ነበርን። አብራሪው በሚሽገን ሐይቅ እና በውስኮንሰን መካከል ነጎድጓዳማ ዝናብ እንዳለ አስታወቀን። መንገጫገጩን ለማስወገድ ወደ ምዕራብ በኩል መስመር ቀየረ።

ከአውሮፕላኑ በስተ ምስራቅ በኩል እየተመለከትኩ ሳለ በድንገት በጨለማው መሃል ደማቅ ነጭ ብርሃን መጥቶ ሰማዩን ሞላው፤ ከዚያም ከአውሮፕላኑ ስድስት ኪ.ሜ. በታች ደመናዎች ተከፍለው ወደቁ እና ተሰወሩ።

ከሰከንድ በኋላ ሌላ ነጭ ብርሃን በሰሜን እና ደቡብ በኩል ብልጭ ብሎ ጠፋ። ጥቂት ቆይቶ መብረቆች ያለ ማቋረጥ በቅርብና በሩቅ መባረቅ ጀመሩ።

ተቀምጬ በመገረም ጭንቅላቴን ስነቀንቅ ነበር። አቤቱ! እነዚህ ሰይፍህን ስትስል የሚወጡ ፍንጣቂዎች ብቻ ከሆኑ፣ አንተ የምትመጣበት ቀን እንዴት ይሆን! የክርስቶስን ቃላት አስታወስኩ፦ “መብረቅ በርቆ ሰማዩን ከዳር እስከ ዳር እንደሚያበራ፣ የሰው ልጅም በሚመጣበት ቀን ልክ እንደዚሁ ይሆናል” (ሉቃስ 17፥24)።

ያንን ክስተት አሁን ላይ ዞር ብዬ ሳስታውስ፣ ክብር የሚለው ቃል ስሜቱ ይወረኛል። ደጋግሜ እርሱን እንድፈልገውና እንድሻው፣ ደግሞም በእርካታ ገበታ ላይ እንድቀመጥና ለክብር ንጉሥ እንድሰግድ ልቤን ስላነሣሣ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። ትልቅ ድግስ ተደግሷል። ሁላችሁም ተጋብዛችኋል!