እኛ ሁላችን በአንድ ወቅት የሥጋችንን ምኞት እያረካን፣ መንገዱንም እየተከተልን በመካከላቸው እንኖር ነበር፤ እንደ ሌሎቹም የቍጣ ልጆች ነበርን። ነገር ግን በምሕረቱ ባለጠጋ የሆነ እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ፣ በበደላችን ሙታን ሆነን ሳለ፣ በክርስቶስ ሕያዋን አደረገን፤ የዳናችሁት በጸጋ ነው። (ኤፌሶን 2፥3-5)
መልአኩ ገብርኤል “የተወደድህ/ሽ ሆይ” ቢላችሁ ደስ አይላችሁም?
ይህ ለዳንኤል ሦስት ጊዜ ሆኖለታል።
- “አንተ እጅግ የተወደድህ ስለ ሆንህ፣ ገና መጸለይ ስትጀምር መልስ ተሰጥቶአል፤ እኔም ይህን ልነግርህ መጣሁ” (ዳንኤል 9፥23)።
- “እጅግ የተወደድህ ዳንኤል ሆይ፣ አሁን ወዳንተ ተልኬአለሁና፣ የምነግርህን አስተውል፤ ቀጥ ብለህም ቁም” አለኝ (ዳንኤል 10፥11)።
- “‘እጅግ የተወደድህ ሰው ሆይ፤ አትፍራ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን፤ በርታ፤ ጽና’ አለኝ” (ዳንኤል 10፥19)።
ሙሉ መጽሐፍ ቅዱሴን እያነበብኩ ሁሌ እነዚህ ጥቅሶች ጋር ስደርስ፣ ወስጄ ለራሴ ማድረግ እንደምፈልግ አልክድም። እግዚአብሔር “እጅግ ተወደሃል” ሲለኝ መስማትን እፈለጋለሁ።
በእርግጥም ደግሞ እሰማለሁ። እናንተም ልትሰሙት ትችላላችሁ። በኢየሱስ የምታምኑ ከሆነ፣ እግዚአብሔር ራሱ በቃሉ “እጅግ ተወዳችኋል” ይላችኋል። የእርሱ ቃል ደግሞ አንድ መልአክ ከሚናገረው የበለጠ እርግጥ እና ጽኑ ነው።
ይህም በኤፌሶን 2፥3-5፣ 8 ላይ ተቀምጧል፦ “እኛ ሁላችን በአንድ ወቅት የሥጋችንን ምኞት እያረካን፣ መንገዱንም እየተከተልን በመካከላቸው እንኖር ነበር፤ እንደ ሌሎቹም የቍጣ ልጆች ነበርን። ነገር ግን በምሕረቱ ባለጠጋ የሆነ እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ፣ በበደላችን ሙታን ሆነን ሳለ፣ በክርስቶስ ሕያዋን አደረገን፤ የዳናችሁት በጸጋ ነው። . . . በእምነት፣ በጸጋ ድናችኋልና።”
“ታላቅ ፍቅር” የሚለውን አስደናቂ ሐረግ ጳውሎስ የተጠቀመው እዚህ ጋር ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ከመልአክ ድምጽ እጅግ ይበልጣል። ኢየሱስ እውነት፣ ሕይወት፣ መንገድ እንደሆነ ካመናችሁ እና ከሁሉ የላቀ ሃብታችሁ አድርጋችሁ ከያዛችሁት፣ በእርግጥም “ሕያዋን” ናችሁ፣ በ”ታላቅ ፍቅር”ም ተወዳችኋል ማለት ነው። የአጽናፈ ዓለሙ ሁሉ ፈጣሪ በሆነው በታላቁ እግዚአብሔር፣ በእጅጉ ተወድዳችኋል። እስቲ አሰላስሉት! እንዲህ ባለ ታላቅ ፍቀር መወደድ ምነኛ መታደል ነው!