“ጠባቂዎች አሏችሁ፤ ሄዳችሁ በምታውቁት መንገድ አስጠብቁ።” (ማቴዎስ 27፥65)
ኢየሱስ ሞቶ ትልቅ ድንጋይ አንከባለው ዘግተው በተቀበረ ጊዜ፣ ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ መጥተው ድንጋዩን ለማተም እና መቃብሩን ለመጠበቅ ፈቃድ ጠይቀው ነበር።
ልፋታቸው ከንቱ ቢሆንም፣ ኢየሱስ ሞቶ እንዲቀር የሚችሉትን ሁሉ ሞክረዋል።
ያኔም ተስፋ-ቢስ ጥረት ነበር፣ ዛሬም ተስፋ-ቢስ ጥረት ነው። ደግሞም ሁልጊዜ ተስፋ ቢስ ሆኖ ይቀጥላል። ሰዎች ባላቸው አቅም ሁሉ ሊሞክሩ ይችላሉ፣ ነገር ግን ኢየሱስን ይዘው ሊያስቀሩት አይችሉም። ማንም እርሱን እንደተቀበረ ሊያቆየው አይችልም።
ይህንን መረዳት ደግሞ አይከብድም። ተገዶ ስላልገባ፣ በወደደው ሰዓት እና ጊዜ መውጣት ይችላል። እንዲያዋርዱት፣ እንዲያዋክቡት፣ እንዲደበድቡት፣ እንዲንቁት፣ እንዲያንገላቱትና እንዲገድሉት ራሱን አሳልፎ የሰጠው በፈቃዱ ነው።
መልሼ ለማንሣት ሕይወቴን አሳልፌ ስለምሰጥ አባቴ ይወደኛል። ሕይወቴን በራሴ ፈቃድ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ አሳልፌ ለመስጠትም ሆነ ለማንሣት ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ የተቀበልሁትም ከአባቴ ነው።
(ዮሐንስ 10፥17–18)
ማንም ይዞ ሊያስቀረው አይችልም፣ ማንም በገዛ ጉልበቱ አልረታውም። ዝግጁ ሲሆን ራሱን ሰጠ።
ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተቀበረ ሲመስል፣ ኢየሱስ ግን በጨለማ ውስጥ አስደናቂ ነገርን እያደረገ ነው። “የእግዚአብሔር መንግሥት ይህን ትመስላለች፤ አንድ ሰው መሬት ላይ ዘር ይዘራል። ሰውየው ሌሊት ይተኛል፤ ቀን ይነሣል፤ ነገር ግን እርሱ ሳያውቅ ያ ዘር በቅሎ ያድጋል” (ማርቆስ 4፥26-27)።
ዓለም ኢየሱስን እንዳበቃለትና እንደተወገደ አስቦ ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ በጨለማ ሥፍራዎች ውስጥ እየሠራ ነበር። “የስንዴ ቅንጣት መሬት ላይ ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች” (ዮሐንስ 12፥24)። “ከእኔ ማንም [ሕይወቴን] አይወስዳትም” ካለና እንዲቀበር ራሱን ፈቅዶ ከሰጠ፣ ያ ማለት በወደደው ጊዜና ቦታ በስልጣን ይወጣል ማለት ነው — “እንደገና ለማንሣት ሥልጣን አለኝ” ብሏል።
“እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አስወግዶ አስነሣው፤ ሞት ይዞ ሊያስቀረው አልቻለምና” (የሐዋርያት ሥራ 2፥24)። ኢየሱስ ዛሬ “በማይጠፋ የሕይወት ኀይል” ክህነት አለው (ዕብራውያን 7፥16)።
ለ20 ምዕተ-ዓመታት፣ በከንቱ ቢሆንም ዓለም የተቻላትን አድርጋለች። ነገር ግን ቀብራ ልታስቀረው ወይም ልታፍነው ወይም ዝም ልታሰኘው ወይም ልትገድበው አልቻለችም። ኢየሱስ ሕያው ነው። ደግሞም ወደ ወደደበት ለመሄድና ለመምጣት ፍጹም ነፃ ነው።
ስለዚህ ምንም ሆነ ምን እርሱን እመኑት፤ ከእርሱም ጋር ሂዱ። በመጨረሻ ልትሸነፉ፣ ልትረቱ አትችሉም።