የተፈጠራችሁት ለእግዚአብሔር ነው | ነሐሴ 19

“እግዚአብሔር የራሱ ሕዝብ ያደርጋችሁ ዘንድ ስለ ወደደ፣ ስለ ታላቅ ስሙ ሲል እግዚአብሔር ሕዝቡን አይተውም” (1ኛ ሳሙኤል 12፥22)

የእግዚአብሔር ስም ብዙውን ጊዜ የሚያመለክተው መልካም ስሙን፣ ዝናውንና ገናናነቱን ነው። በተለምዶውም፣ አንድ ሰው ስሙን እያስጠራ ነው ስንል፣ “ስም” የሚለውን ቃል የምንጠቀምበት መንገድ ከዝናና ታዋቂነት ጋር በተገናኘ ይሆናል ማለት ነው። ወይም አንዳንድ ጊዜ ይህ “ስም” የታዋቂ ምርት መለያ (brand) ስም ነው እንላለን። ትልቅ ስምና ዝና ያለው የምርት ስም ማለታችን ነው። በ1ኛ ሳሙኤል 12፥22 ላይ እግዚአብሔር እስራኤልን “የራሱ ሕዝብ” እንዳደረገና “ስለ ታላቅ ስሙ ሲል እግዚአብሔር ሕዝቡን” እንደማይተው ሳሙኤል ሲናገር፣ ይህንን እያለ ይመስለኛል።

እግዚአብሔር ለስሙ ያለው ይህ ዐይነት ቅንዓት በሌሎች በርካታ ምንባቦች ውስጥ ተረጋግጧል።

ለምሳሌ፣ በኤርምያስ 13፥11 እግዚአብሔር ክብሩን ለማጉላት እንደተመረጠ መቀነት ወይም ቀበቶ አድርጎ እስራኤልን ገልጿታል፤ ምንም እንኳ እስራኤል ለጊዜው ብቁ ያልነበረችበት ጊዜ ቢሆንም። “መቀነት በሰው ወገብ ላይ እንደሚታሰር፣ መላው የእስራኤልና የይሁዳ ቤት ከእኔ ጋር ተጣብቆ ለስሜ ምስጋናና ክብር፣ የኔ ሕዝብ እንዲሆንልኝ አድርጌው ነበር፤ ሕዝቤ ግን አልሰማም’ ይላል እግዚአብሔር።” እስራኤል ለምን የእግዚአብሔር መቀነት ሆና ተመረጠች? ለእግዚአብሔር “ስም፣ ምስጋና እና ክብር” እንድትሆን ነው።  

“ስም” የሚለው ቃል ምንን ለመወከል እንደገባ በዚህ ዐውድ ውስጥ “ምስጋና” እና “ክብር” የሚሉትን ቃላት በመመልከት ማወቅ እንችላለን። “ዝና” ወይም “ገናናነት” ወይም “መልካም ስም” ማለት እንደሆነ ይጠቁማሉ። እግዚአብሔር እስራኤልን የመረጠው ሕዝቡ መልካም ስምና ዝናን እንዲያመጡለት ነው። እግዚአብሔር በኢሳይያስ 43፥21 ላይ ስለ እስራኤል ሲናገር፤ “ለራሴ ያበጀሁት ሕዝብ ምስጋናዬን ያውጅ ዘንድ” ነው ይላል።

ከዚያ ደግሞ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛዋ እስራኤል እንደሆነች ግልጽ ከሆነ በኋላ፣ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ዓላማ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፦ “እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ፣ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ለራሱ የለያችሁ ሕዝብ ናችሁ” (1ኛ ጴጥሮስ 2፥9)።

በሌላ አነጋገር እስራኤል እና ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር የተመረጡት በዓለም ላይ ስሙን እንዲያስጠሩለት ነው። ለዚህ ነው ከሁሉ በፊት “ስምህ ይቀደስ” ብለን የምንጸልየው (ማቴዎስ 6፥9)። ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ እንዲመራን የምንለምነውም ለዚህ ነው (መዝሙር 23፥3)።

ሁሉ ነገሩ እግዚአብሔር የሆነለት ሕዝብ መሆናችንን የምንናገርበት ምክንያት ራሱ እግዚአብሔር ሁሉ ነገሩ እግዚአብሔር ስለሆነለት ነው። እኛም በዚህ እውነት ተስማምተን ተባብረናል። ከመስቀሉ ታሪክ በዚህኛው በኩል ላለን ለእኛ ደግሞ፣ በክርስቶስ ላይ የተመሰረተ ሕዝብ መሆን ማለት ክርስቶስን ከፍ የሚያደርግ ሕዝብ መሆን ማለት ነው። “ልጆች ሆይ፤ ኀጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና፣ እጽፍላችኋለሁ” (1ኛ ዮሐንስ 2፥12)። “በእርሱ በኩል ለእግዚአብሔር አብ ምስጋና እያቀረባችሁ፣ በቃልም ሆነ በተግባር የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት” (ቆላስይስ 3፥17)።