በዲጅታል ዘመን ልጆችን ለማሳደግ የሚጠቅሙ 12 ጠቃሚ ምክሮች

iGen ማነው?

በስድስት እና በሃያ ሦስት ዓመት መካከል የሚገኙ ታዳጊዎችና ወጣቶች ድህረ ሚሊኒየም ፣ Gen Z ወይም iGen የሚባል መጠሪያ ተሰጥቷቸዋል። በዚህ ትውልድ ላይ የተደረጉ ጥናቶችን በማየት ለመጋቢዎች፣ ለመሪዎች እንዲሁም ለወላጆች የሚያስተላልፈውን መልእክት እንድታስተውሉ እፈልጋለሁ። በዚህ የዲጂታል ዘመን ታዳጊዎችን እንዴት እንቅረጽ?

እውነት ለመናገር ስለ ትውልድ ጠቅልሎ ከመናገር እና በጥናት የተገኙ መረጃዎችን በቸልተኝነት ከማለፍ የትኛው ይበልጥ ኀጢአት እንደሆነ አላውቅም። በእግዚአብሔር እርዳታ ሁለቱንም ላለመፈጸም እንሞክራለን።

iGen በ1995 እና 2012 መካከል ለተወለዱ ሰዎች የተሰጠ ስያሜ ነው። ወደ 74 ሚሊዮን ወይንም 24% የሚሆነው የአሜሪካ ሕዝብ በዚህ መሐል ይገኛል። በአሜሪካ ታሪክም እጅግ የተለያየ የሆነው እንዲሁም ከዘመናዊ ስልክ እና ከኢንተርኔት መረብ ጋርም ሱስ የያዘው ይህ ትውልድ ነው። የiGen ታዳጊዎች ኢንተርኔት በ1995 ለሕዝብ ይፋ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የተወለዱ ናቸው። ከኢንተርኔት ውጪ ሌላ የመረጃ ምንጭ የላቸውም። ወደ ጉልምስናም የተቀላቀሉትን በዚሁ ዘመናዊ ስልኮች በተስፋፉበት ወቅት ነው። እንደ ወላጅ እነዚህን ታዳጊዎች ለማሳደግ ብዙ ችግሮች ያጋጥሙናል።

በታዳጊዎች ዘንድ ያሉ አዝማሚያዎች

በሳን ዲያጎ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው የስነ አእምሮ ሃኪም ጄን ትዌንግ ስለ iGen ብዙ ስልታዊ ጥናቶችን ካካሄዱ ምሁራኖች አንዷ ነች። ለጥናቱ የሚያስፈልጉትን መረጃዎች ከቃለ መጠይቅ እና ከሌሎች ምንጮች በማሰባሰብ፣ “በእውነት ዘመናዊ ስልኮች ትውልድን አጥፍተዋልን?” የሚል መጣጥፍ ለሕዝብ አቅርባ ነበር። ይህ ጽሑፍ፣ “የiGen ታዳጊዎች እርስ በርስ እጅግ የተሳሰሩት ለምንድን ነው? ተቃዋሚ ያልሆኑ፣ ሁሉን አቃፊ የሆኑ፣ ደስተኛ ያልሆኑ እና ለአዋቂነት ዕድሜ ፈጽሞ ያልተዘጋጁ የሆኑትስ ለምንድን ነው?” ከተባለው መጽሐፍ የተቀነጨበ ነበር።

ቶም ሃንክስ “big” በተባለው ፊልም ላይ የሚገኙትን ትውልዶች፣ “ጎልማሳ ለመሆን ትዕግሥት ያጡ ሕጻናት” ካለው በተቃራኒ iGen ወደ ጎልማሳነት ላለመለወጥ የተቻላቸውን የሚያደርጉ ልጆች ናቸው።

የትዌንግ ሰፊ ጥናት እንደሚያመለክተው በዚህ ዘመን የተወለዱ ታዳጊዎች ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንደሆነ ያሳያል። ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ በትምህርት ቤት ውስጥ በመሣሪያ ተጠብቀው ያደጉ የመጀመሪያ ትውልድ ናቸው። በወላጆች በጣም ተጠብቀው እንዲሁም ምርጫቸው ተከብሮ ያደጉ ትውልድ ናቸው። ሁሉንም ማስረጃዎች አንድ ላይ በማሰባሰብ፣ የiGen ታዳጊዎች አብሮ ለመሆን የሚመቹ ናቸው ማለት እንችላለን። ካለፉት ትውልዶች ጋር ሲነጻጸር የiGen ታዳጊ ወጣቶች ወደ ጭፈራ ቤቶች የመሄድ፣ ከተቃራኒ ጾታ ጋር የፍቅር ግንኙነት የመጀመር፣ መንጃ ፍቃድ ለማግኘት የመወዳደር፣ አልኮል የመጠጣት፣ ሲጋራ የማጨስ፣ የደኅንነት ቀበቶ በሌለበት መኪና የመሳፈር ወይም ግብረ ሥጋ ግንኙነት የመሞከር ዕድላቸው አነስተኛ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። .

አብዛኞዎቹ የiGen አዝማሚያዎች ጥሩ ናቸው። መልካም ካልሆኑ ባሕርያት በመራቃቸው መደሰት አለብን።  ነገር ግን ትዌንግ እንደምትለው፣ እነዚህ አዝማሚያዎች አንድ ላይ ሆነው፣ ረጅም በታዳጊነት አስተሳሰብ ውስጥ የመቆየትና ያጠረ የአዋቂነት ጊዜን ያስከትላሉ።

አምስት የ iGen መለያዎች

ከዚህ የዘገየ የጎልማሳነት ጊዜ እና ረጅም የታዳጊነት ጊዜ በተጨማሪ iGen ሌሎች መለያዎች አሏቸው

1. ዘመናዊ ስልኮችን በመጠቀም ብዙ ጊዜ ያሳልፋሉ።

አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ በአሜሪካ ውስጥ ሕፃናት የመጀመሪያውን ዘመናዊ ስልክ የሚያገኙበት አማካይ እድሜ 10.3 ዓመት ነው። አብዛኛዎቹ የእነዚህ ታዳጊዎች ስልክ፣ ቤተ ሰቦቻቸው ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ስልኮች ሲሆኑ ነገር ግን ከ12 እስከ 17 ዓመት ዕድሜ ያሉት 80% የሚሆኑት የዘመናዊ ስልክ ተጠቃሚዎች ናቸው።

2. ሁልጊዜ ኢንተርኔት ይጠቀማሉ።

የiGen ታዳጊዎች ለሥራ፣ ለበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት እና በትምህርት ቤት የተሰጣቸውን የቤት ሥራ ለመሥራት ከሚጠቀሙት ጊዜ ይልቅ በቤታቸው ኢንተርኔት በመጠቀም የሚያጠፉት ጊዜ ይበልጣል። በጓደኛ እና በተቃራኒ ጾታ ግፊት ሁልጊዜ ጊዜያቸውን ኢንተርኔት ላይ ያጠፋሉ።

3. ለመንፈሳዊነት ጊዜ የላቸውም።

ከአራት የiGen ታዳጊ ወጣቶች አንዱ በየትኛውም የሃይማኖታዊ አገልግሎቶች ላይ አይገኝም ወይም ማንኛውንም ዐይነት የግል መንፈሳዊ ሕይወት የለውም። “iGen ከዚህ በፊት ከነበሩት ከየትኛውም ትውልድ የበለጠ ሃይማኖት በሌላቸው ወላጆች የማደግ ዕድላቸው ሰፊ ነው።” (Twenge, 121) በዚህ ትውልድ ውስጥ ብዙ አማኞች ቢኖሩም ከአራቱ አንዱ ግን ሃይማኖት የለውም።

4. እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነት በአነስተኛ መላመዶች ይገነባሉ።

የiGen ታዳጊዎች ትንሽ እና ያልተሟሉ የማኅበራዊ ሚዲያ መረጃዎችን ለምሳሌ ምስሎችን፣ ትዊቶችን፣ አጭር የጽሑፍ መልእክቶችን በመጠቀም አንደኛቸው ለሌላኛቸው ያላቸውን መረዳት ይቀርጻሉ (Smarter Than You Think, 209–244)። ይህንን ክህሎት ክላይቭ ቶምፕሰን “የአካባቢ ግንዛቤ” ሲል ጠርቶታል። በኢንተርኔት መረብ የተዋወቅሁትን ሰው በአካል ካወቅሁት ማንነት ጋር ማዛመድ ለእኔ እንግዳ ነገር ነው። ይህ ነገር ግን ለታዳጊዎች ቀላል ነው። የተለያየ ቦታ ቢሆኑም “አካባቢያቸውን በመገንዘብ” በስክሪኖች በኩል ይገናኛሉ። አንዳቸው ለአንዳቸው ያላቸው መረዳት ሙሉ ባልሆኑ የዲጂታሉ ዓለም መረጃዎች ላይ የተመሠረተ ነው።

5. የነቁ ናቸው።

ትዌንግ ሚሌንያልስ (ከ1981 እስከ 1996 የተወለዱ ልጆች) የተባሉት “ብሩህ አመለካከት አላቸው” ሲሉ በታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት ወቅት ያደጉት የiGen ታዳጊዎችን ግን “ተስፋ ለመቁረጥ የቀረቡ፣ ለማኅበራዊ ውጥረት የተጋለጡ እና ለጉዳት ተጋልጠዋል ላሉት ደግሞ እንክብካቤንና ጥበቃን መስጠት የሚፈልጉ ናቸው” በማለት በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት አስቀምጠዋል። በፓርክላንድ ሰልፍ፣ ለሕይወታችን እንቅስቃሴ! (the March for Our Lives)፣ ብሔራዊ የትምህርት ቤት የእግር ጉዞ ቀን(the National School Walkout Day) እና በ #Never Again እንቅስቃሴ ላይ እንደተረጋገጠው እነዚህ ታዳጊዎች ንቁ ናቸው። iGen እንቅስቃሴ የማያበዙ ሲሆኑ ላሰቡት ዓላማ ግን መቆም ይችላሉ። አለን ጃኮብስ “Contemporary Children’s Crusades” በተባለው መጽሐፉ ላይ እንደ ገለጸው ይህ የራሱ ችግር እንዳለው ተናግሯል። በዐሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ወጣቶች የአዋቂዎችን የፖለቲካ አጀንዳዎች ወደ እነርሱ እንዳይመጣ የሚገፉ ናቸው። ሆኖም ግን iGen በማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ንቁ ናቸው። ይህ ደግሞ መጋቢዎችና ወላጆች ከእነዚህ ታዳጊዎች ጋር እንዴት መግባባት እንዳለባቸው ያስረዳል።

iGen ምን ዐይነት ተግዳሮቶች ያጋጥሟቸዋል?

እስካሁን ድረስ፣ ከትዌንግ ምርምር እንዲሁም በሌሎች ምርምሮች የተረጋገጠው የታዳጊዎች አሳሳቢ ችግር ድባቴ ነው። እ.ኤ.አ. በ2012 እና 2015 መካከል ባሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በወንዶች ላይ የድብርት መጠን በ21% ሲጨምር በሴቶች ላይ ደግሞ በ 50% ጨምሯል። ይህ አሃዝ ደግሞ ራስን የማጥፋት መጠን ላይ ተንጸባርቋል። ከ1990 እስከ 2000 ባለው ውስጥ ይህ አሃዝ የቀነሰ ቢሆንም ከ2000 ዓ.ም. በኋላ ግን እንደገና ጨምሯል። እ.ኤ.አ. በ2007 ላይ ከ15 እስከ 19 ዓመት በሆኑት ታዳጊዎች ላይ ከነበረው ራስን የማጥፋት መጠን በ2015 በ46% ጨምሯል። እንዲሁም ከ12 እስከ 14 ዓመት ዕድሜ ባላቸው ሕፃናት ደግሞ ራስን የማጥፋት መጠን በሁለት እጥፍ ጨምሯል። (Twenge, 110)

ትዌንግ “the paradox of iGen: an optimism and self-confidence online that covers a deep vulnerability, even depression, in real life”  በተባለው መጽሐፏ  እንዲህ ብላለች፤ “ላለፉት ዐሥርት ዓመታት iGen የአእምሮ-ጤና ቀውስ አፋፍ የነበረ ትውልድ ነበር ማለት ማጋነን አይሆንም። አብዛኛው የዚህ ምንጭ ደግሞ ስልክ ነው።”(102)

iGen ማን ነው? የነቁ እና አካባቢያቸውን መገንዘብ የሚችሉ ናቸው። በኢንተርኔት መረብ ላይ የራስ መተማመን አላቸው። በጭራሽ ከኢንተርኔት ርቀው አያውቁም። ከሰዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት በቴክኖሎጂ ምሕዳሮች ላይ የተመሰረተ ነው። እንዲሁም ብቸኝነታቸውንና ሕይወታቸው ትርጉም አልባ እንዲሆንባቸው የሚያደርጋቸው ከሰዎች ጋር ያላቸው ንጽጽር የሚቀዳው ከዚሁ ቴክኖሎጂ ነው። ወላጆች ይህንን በአብዛኛው ያውቃሉ። ስለ iGen መጽሐፍ ከመጻፉ ከረጅም ጊዜ በፊት እነዚህን ችግሮች አይተዋል።

ለ iGen ወላጆች ዐሥራ ሁለት ምክሮች

ስለ ታዳጊዎች እና ስክሪኖች ስንናገር ተጨባጭ እና መሬት የወረዱ ሐሳቦች መነሣት አለባቸው። ስለዚህ በቤተ ክርስቲያናችሁ እና በቤቶቻችሁ ውስጥ የምታደርጓቸውን ውይይቶች መሠረት በማድረግ ዐሥራ ሁለት ተግባራዊ ምክሮችን ላቅርብ።

1. ማኅበራዊ ሚዲያን በተቻለ መጠን ማዘግየት።

ማኅበራዊ ሚዲያ ታዳጊዎች ውዝግብ ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል። ጋዜጠኛ ናንሲ ጆ በጻፈችው “የአሜሪካ ልጃገረዶች፡ ማኅበራዊ ሚዲያ እና የታዳጊዎች ምስጢራዊ ሕይወት” በተሰኘ አስገራሚ መጽሐፍ አንዲት ታዳጊ፣ “ማኅበራዊ ሚዲያ ሕይወታችንን እየጎዳ ነው” ስትል ገልጻለች። በመቀጠልም ሴልስ፣ “ታዲያ ለምን አታቆሚም?” ብላ በምትጠይቃት ጊዜ የታዳጊዋ ምላሽ፣ “ምክንያቱም ሌላ ሕይወት የለንም” የሚል ነበር (ሴልስ፣ 18)። ማኅበራዊ ሚዲያ ታዳጊዎች ሕይወትን የሚፈልጉበት ቦታ ነው። በዚህም ሕይወታቸውን የሚያጡበት ቦታ ይሆናል። ይህንን የተገላቢጦሽ አስተሳሰብ ልጆቻችን እንዲገነዘቡት ማድረግ ያስፈልጋል። ጥበብ የጎደለው የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል።

2. ዘመናዊ ስልኮችን በተቻለ መጠን ማዘግየት።

አንዴ ልጅዎን የጽሑፍ መልእክት እና እንደ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ስናፕቻት የተባሉ መተግበሪያዎች ያሉት ዘመናዊ ስልክ ካስተዋወቁት በኋላ ልጅዎን መቆጣጠር እጅግ አስቸጋሪ ነው። ይህ እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳለሁ።

ልጆቻችሁ ወሲባዊ ለሆኑ ንግግሮች እና እርቃን ለሚያሳዩ ፎቶዎች ሊጋለጡ ይችላሉ፤ ደግሞም ይህንን እንደ ወላጅ በጭራሽ ላያውቁት ይችላሉ። ሴልስ በመጽሐፏ፣ ሴት ታዳጊ ወጣቶች ወንዶች ለእነርሱ ያላቸውን ፍላጎት ለማሳየት የእርቃን ፎቶ እንደሚልኩላቸው እናም ወንዶች ብዙውን ጊዜ በምላሹ የእነርሱን የእርቃን ምስሎች እንደሚጠይቁ ለማረጋገጥ ችላለች። ይህ ከመከሰቱ በፊት ልጆቻችንን ማስጠንቀቅ እንዳለብን ግልጽ ነው። ነገር ግን ልጅዎ ፈልጎ እንኳን የእርቃን ምስሎችን ባያመጣቸውም በተለያዩ ማኅበራዊ ሚድያዎች ለልጅዎ የሚመጣውን መከልከል አይችሉም። 47% የሚሆኑ ወጣቶች ስናፕቻት ይጠቀማሉ። ይህ መተግበሪያ በተመደበለት ደቂቃ የሚጠፋ ምስሎች ለመላክ እና ለመቀበል ታዳጊዎች ይጠቀሙታል። በዘመናዊ ስልክ ዘመን ወሲባዊ የሆኑ ጽሑፎችን መላላክ የተለመደ ሆኗል። ዘመናዊ ስልኮች እጅግ ኀይለኛ መሣሪያዎች ናቸው። ለልጅዎ ይህንን ለመስጠት ያለውን ግፊት ይቋቋሙ። በተጨማሪም የማትጠቀሙበትን ስልክ በቤታችሁ አትተዉ።

3. በቤቱ ውስጥ ያለውን ዋይፋይ ተቆጣጠሩ።

በእኛ ቤት ዋይፋይ ካላስፈለገን አናበራውም። አብዛኞቹ ራውተሮች ዋይፋዩን በፈለግንበት ሰዓት ማቆም እንድንችል ይፈቅዱልናል። “The Circle” የሚባል መሣሪያ ከራውተራችን አጠገብ የሚቀመጥ መሣሪያ ሲሆን በፈለግነው ሰዓት ዋይፋዩን እንድናጠፋው እንዲሁም በጊዜ ገደብ፣ በመኝታ ሰዓት እና በይዘት ዐይነት የፈለግነውን መርጠን ዋይፋዩን መቆጣጠር እንድንችል ይረዳናል። በዋይፋዩ እና ዋይፋዩን በሚጠቀመው ኮምፒውተር ወይንም ስልክ መካከል ያለ መሣሪያ ነው። ዋይፋዩን በሚጠቀመው ሁሉም መሣሪያዎች ላይ የወላጅ መቆጣጠርያ መተግበሪያ ከመጫን ይልቅ ወደ መሣሪያዎቹ የሚገባውን የመረጃ ፍሰት መቆጣጠር እንችላለን። በስልኬ 2 ዘመናዊ ቴሌቪዥን 3 ኮምፒውተር፣ አይፖድ እና አይፓድ የሚጠቀሙትን ዋይፋይ ማቆም እችላለሁ። ይህ እጅግ አስገራሚ ነው። በቤት ውስጥ ያሉ ልጆች ዋይፋዩን መጠቀም ሲፈልጉ ለምን መጠቀም እንደፈለጉ ተናግረው መጠቀም ይችላሉ። እዚህ ላይ ብዙ ማለት ይቻላል ነገር ግን ይህ መሣሪያ ለምንጠቀመው ዋይፋይ ግልጽ የሆነ ዓላማ ይሰጠዋል። ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን ዋይፋይ ሁልጊዜ የማይበራ ከሆነ ነው።

4. ከቤት ውጪ ከሰዎች ጋር ዘመናዊ ስልክን ሳይጠቀሙ ይተዋወቁ።

ከ6 እስከ 12 ዕድሜ ላሉ ሕጻናት እንደ ቨራይዘን ጊዝሞ ያሉ ዘመናዊ ሰዓቶችን መጠቀም ይችላሉ። ጊዝሞ በወላጅ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ ስልክ መደወልና መቀበል የሚችል ዘመናዊ ሰዓት ነው። ይህ ሰዓት ከወላጅ ስልክ ጋር በመተግበሪያ የተገናኘ ጂፒኤስ የተገጠመለት ሲሆን ልጅዎ የት እንዳለ ያሳያል።

ወላጆች ስልክን ለሦስት ነገር ይፈልጋሉ። (1) በፈለጉት ሰዓት ልጆቻቸውን ለማግኘት (2) ልጆቻቸው በፈለጓቸው ሰዓት እንዲያገኟቸው (3) ልጃቸው የት እንደሆነ በጂፒኤስ አማካኝነት ለማወቅ እነዚህን ጥቅሞች ለማግኘት ዘመናዊ ስልክ የግድ አያስፈልግም። ጊዝሞ እነዚህን ሦስት ነገሮች መስጠት ይችላል። ከ13 ዓመት በላይ ለሆኑት ደግሞ ፍሊፕ ፎን የሚባለውን ስልክ መጠቀም ይቻላል። ይህ ስልክ ዋጋው ቅናሽ ነው። አንድ ጊዜ ባለቤቴ ወደ ስልክ ቤት ስትሄድ፣ “የማይረባውን ስልክ ስጠኝ” ብለህ ለሻጩ ጠይቅ ያለችኝን አልረሳውም።

5. በየመቱ ለልጅዎ የሚሰጡትን የቴክኖሎጂ መሣሪያ በደረጃ ያስቀምጡ።

ወላጆች አብዛኛውን ጊዜ የሚሠሩት ስሕተት ዘመናዊ ስልክ፣ ሌላውን ሕይወት የማይነካ ብቻውን የተለየ ትንሽ መሣሪያ ብቻ አድርገው ማሰባቸው ነው። ይህ ግን እውነት አይደለም። ዘመናዊ ስልክ አንድ ልጅ ከተወለደበት ጊዜ አንሥቶ ከተፈጠሩት የመገናኛ ቴክሎሎጂዎች ሁሉ ቁንጮ ነው። ዘመናዊ ስልክ ማግኘት ማለት ቀደም ብሎ ከነበሩት የቴክኖሎጂ ደረጃዎች የተሻለ የሆነውን እንደ መሸለም ነው።

እኔና ባለቤቴ እነዚህን ደረጃዎች በዚህ መልኩ አስቀምጠናቸዋል። ወደ ቤታችሁ የቤት ዋይፋይ ካስገባችሁ፣ ልጆቻችሁ በቤት ውስጥ ብቻ ሊጠቀሙት የሚችሉትን ቴክኖሎጂ ማስተዋወቅ ትችላላችሁ። በወረቀት ላይ አንድ ትልቅ ሳጥን ይሣሉ። በወረቀቱ የላይኛው የግራ ክፍል ላይ 0 ዕድሜ ብለው ይጻፉ፤ በላይኛው የቀኝ ክፍል ደግሞ 18 ዓመት ብለ ይጻፉ። ከግራ ወደ ቀኝ ልጅዎ ለተለያዩ ቴክኖሎጂዎች የሚተዋወቅበት የመጀመሪያዎቹ 18 ዓመታት ናቸው። በመቀጠልም ከታችኛው ግራ የወረቀቱ ክፍል ወደ ላይኛው ቀኝ የሚሄድ ደረጃ ይሣሉ። በዚህ የደረጃ ሥዕል ላይ የሆነ ጊዜ ላይ ሥዕልና ትምህርታዊ ጨዋታዎች ያሉበትን ታብሌቶች ለልጅዎ ሊያስተዋውቁ ይችላሉ። ይህ ጊዜ ደግሞ ልጅዎ ከ 3 እስከ 8 ዓመት የሞላበት ጊዜ ሊሆን ይችላል። ከአንድ ደረጃ በኋላ ደግሞ ትምህርታዊ ቪዲዮዎች ያሉትን ታብሌት ልጅዎ 6 ዓመት እያለ ሊያስተዋውቁት ይችላሉ። በቀጣዩ ደረጃ ደግሞ ልጅዎ 10 ዓመት ሲሞላው የተለያዩ የቤት ሥራዎችንና ፕሮጀክቶችን እንዲሠራ የቤተሰብ ኮምፒውተር ሊሰጡት ይችላሉ። ቀጥሎ ደግሞ እንደ ጊዝሞ ወይንም ፍሊፕ ያለ ስልክ ሊሰጡት ይችላሉ። 12 ዓመት ሲሞላው ደግሞ የተለያዩ ጥያቄዎችን እንዲጠይቅ ጉግልን እንዲጠቀም ሊፈቅዱ ይችላሉ። ቀጥሎም ከተመረጡ ጓደኞች ጋር እንዲገናኝ እንደ ፌስቡክ ያሉ ማኅበራዊ ሚድያዎችን ሊፈቅዱ ይችላሉ። በመጨረሻም በ15 ወይም በ16 ወይም 17 ዕድሜ ላይ ዘመናዊ ስልክ ሊሰጡት ይችላሉ። እኔ ግን 18ን እመርጣለሁ፤ ይህ የእኔ ሐሳብ ነው እርሶ ግን ለልጅዎ መወሰን ይችላሉ።

የዚህን ጥቅም በሁለት መልኩ ልንረዳው እንችላለን፦

  • እንደ አስፈላጊነቱ ለልጅዎ ያዘጋጁለትን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ደረጃ ማሳደግና በዚህም የዕቅድ ዐውድ ውስጥ ዘመናዊ ስልክ እንዴት መጠቀም እንዳለበት ማስረዳት ይችላሉ። በቤት ውስጥ ባለው የዋይፋይ አጠቃቀም ታማኝነቱን ካሳየ ከቤት ውጪ ስልክ ወደ መያዝ ደረጃ መምጣት ይችላል። ይህ ደግሞ በትንሽ ነገር መታመን በትላልቅ ነገሮች ላይ እንዲታመን እንደሚያደርገው ያሳየዋል።
  • የሞባይል ዳታ ያለው ዘመናዊ ስልክ አንዴ ለልጅ ከሰጡ በኋላ ጠንካራ ቁጥጥር ከነበረው የኢንተርኔት አጠቃቀም ምንም ወደሌለው እየተሸጋገሩ እንደሆነ ለወላጆች ያሳስባል። በግራ በኩል ባሉት (በቤት ውስጥ ያለው ዋይፋይ) እና ዘመናዊ ስልክ ባለበት በቀኝ (በፈለጉት ጊዜና ቦታ ኢንተርኔትን በስልክ መጠቀም) መካከል ደማቅ መስመር መሳል ይችላሉ። ይህ መስመር ትልቅ ሽግግርን ያመለክታል።

6. ለሁሉም ዕድሜዎች እና ለሁሉም የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች የሚሆን ዐብይ መመሪያ፡- ስክሪኖች ከመኝታ ክፍሎች ውጪ ይቀመጡ።

 ቢያንስ ለ12 ሰዓታት ለምሳሌ ከጠዋት 2 ሰዓት እስከ ማታ ሁለት ሰዓት ስክሪኖችን ከመኝታ ክፍሎች ውጪ እንዲሆኑ ትእዛዝ ያውጡ። ቴሌቭዥኖች፣ የጌም መጫወቻዎች ፣ ታብሌቶች ፣ ላፕቶፖችም ሆኑ ስልኮች መኖር የለባቸውም። የማያልቀውን የማኅበራዊ ሚድያ ጥማትን ማስቆም ይገባል። የጌም ሱሶችን ማስቀረት ይገባል። የእንቅልፍ ሰዓት መጠበቅ አለበት። ሁሉም መገልገያዎች ከልጆች ክፍል ውጪ በሆነ ቦታ ቻርጅ ሲደረጉ ይደሩ። ለዚህ ጥሩ መፍትሔ የሚሆነው በእናትና በአባት ክፍል ውስጥ ቻርጅ ማድረጊያ ቦታ ማመቻቸት ነው።

7. የዘመናዊ ስልኮች (ስማርትፎን) /ኮንትራት/ውል ይፃፉ።

ወደ ዘመናዊ ስልኮች ስንሄድ የሚጠበቁ ባሕርያትን፣ ሰዓት እላፊዎችን እንዲሁም ከስልኩ ጋር ተያይዞ ቤተሰብ የሚጠብቃቸውን ነገሮች ይጻፉ። ልጆች ስልኮቻቸውን ለመጠቀም የሚያስገቧቸውን መረጃዎች እንዲያጋርዎት ያድርጉ። እናም አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ስልኮቹ በጊዜያዊነት ጥቅም ላይ መዋል እንዳይችሉ ማገድ የሚችሉባቸውን መንገዶች ይለማመዱ። ብዙ መተግበሪያዎች ይህንን በቀላሉ ያስረዳሉ። ለልጆቻቸው ያለጊዜው አስቀድመው ዘመናዊ ስልኮችን ለሰጡ ወላጆችም ቢሆን የስልክ ኮንትራት ለማዘጋጀት አልረፈደም።

8. እያንዳንዱ ልጅ ለዲጂታሉ ዓለም እንዴት ምላሽ እንደሚሰጥ ይመልከቱ።

ይህ ለእኔ በጣም አስደናቂ ነበር። እኔና ባለቤቴ ሁለት ልጆችን ጨምሮ ሦስት የiGen ታዳጊዎች አሉን። እያንዳንዳቸው የዲጂታል ሚዲያን በተለያየ መንገድ ይጠቀማሉ። አንዱ ልጄ የዱድ ፐርፌክት (Dude Perfect) ቪዲዮን 40 ጊዜ ያለማቋረጥ በማየት ሰዓታትን ያባክናል። አንደኛዋ ልጄ ደግሞ አዲስ የሙዚቃ መሣሪያ ገዝታ፣ እንዴት ኮርዶችን መቆጣጠር እንዳለባት የሚያስተምሩ የ30 ደቂቃ ነጻ የዩቲዩብ ቪድዮዎችን በመመልከት ታሳልፋለች። ይህንን በኡክሌሌ፣ ከዚያም በኪቦርድ ቀጥሎም ክላርኔትን በመጠቀም በመጨረሻም መደበኛ የሥልጠና ትምህርቶችን እንድትወስድ ምክንያት ሆኗል። ልጆቼ አዳዲስ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ ዩቲዩብ ያለው አስተዋጽዖ ይገርመኛል። ልጆቼ በተቻለ ፍጥነት ከዩቲዩብ አጋዥ ሥልጠናዎች እንዲማሩ እፈልጋለሁ፣ ነገር ግን  ይህ እንዲሆን የምፈልገው ልጆቼ ለዚህ ዝግጁ ከሆኑ በኋላ ነው።

እያንዳንዱ ልጅ በተለያየ መንገድ ለዲጂታሉ ዓለም ምላሽ ይሰጣል። አንዳንድ ታዳጊዎች 5,000 ሰዎችን መከተል እንዲችሉ ማኅበራዊ ሚዲያን ይፈልጋሉ። ሌሎች ታዳጊዎች ደግሞ 5 የቅርብ ጓደኞችን መከተል እንዲችሉ ማኅበራዊ ሚዲያ ይፈልጋሉ። እነዚህ በጣም የተለያዩ የማኅበራዊ ሚድያ አጠቃቀሞች ናቸው። በእነርሱ ውስጥ በሚያዩት ነገር ላይ በመመሥረት እያንዳንዱን ልጅ በልዩ ሁኔታ ያሳድጉ። እናም ልጆቻችሁ ኢ-ፍትሐዊ ነው ብለው ካጉረመረሙም፣ የዲጂታል ደረጃቸውን ያስታውሷቸው። ቤት ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ልጅ ለምን በተለያዩ ደረጃዎች ላይ እንደሚገኝ ያስረዱ።

9. የምናሳድገበት መንገድ የልብ ፍላጎትን በማረም ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት

ዘመናዊ ስልኮች አዲስ ኀጢአትን አይፈጥሩም። በሕይወት ውስጥ ያሉትን ፈተናዎች አጉልተው እጆቻችን ላይ ባሉ ጥራት ባላቸው ስክሪኖች ያቀርቡልናል። ድሮ የነበሩ ፈተናዎችን አዲስ የመሳብ ፣ሱስ የመሆን እና ተደራሽ የመሆንን አቅም ሰጥቶአቸዋል።  ይህም ማለት በዲጂታል ዘመን ወላጆች የሚጨነቁት የታዳጊ ልጆቻቸውን ሐሳብ ስለተቆጣጠሩት ነገሮች ነው። በጣም የሚያስፈራው ይህ ነው። እኛ ወላጆች ሁሌም ልጆቻችን የሚወዱትን ነገር ለማረም ጦርነት ላይ ነን። ነገር ግን የዲጂታል ዘመን የወላጅነት ስንፍናችንን በበለጠ ፍጥነት አጋልጦታል።

ልጆቻችን በክርስቶስ ውስጥ የላቀ እርካታን ማግኘት ካልቻሉ፣ እርካታቸውን ሌሎች ነገሮች ውስጥ ይፈልጉታል። ይህ መልእክት ሁሌም ቢሆን እጅግ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም “ሌሎች ነገሮች” ያልናቸው ነገሮች በዘመናዊ ስልክ ሱስ መልክ እየተገለጡ ነው። የቃላት ጨዋታ እየተጫወትን አይደለም ወይንም ክርስቶስ በእሁድ ቀን የበላይ ነው እያልን አይደለም። የታዳጊ ልጆቻችንን ልብ መንፈስ ቅዱስ እንዲከፍት በየዕለቱ በጸሎት እየቃተትን ነው። ክርስቶስን ከማንኛውም በዲጂታል ዘመን ውስጥ ከሚገኙ ጥቃቅን ነገሮች በላይ ከፍ አድርገው ሊመለከቱት ይገባል። አለበለዚያ እነዚያ ጥቃቅን ነገሮች ያጠፏቸዋል። ለዚያም ነው የምናሳድግበት መንገድ ዛሬም ቢሆን እጅግ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ የሆነው።

10. ዲጂታል ቴክኖሎጂን ልጆችን በትክክለኛው መንገድ ለማሳደግ ይጠቀሙበት

ጥቂት ምሳሌዎችን ነጥሎ እንደ አጠቃላይ የጥበብ ምክር መምከር ብቻ በቂ አይደለም። በዲጂታል ዘመን ታዳጊዎችን ለማሳደግ ቅዱሳት መጻሕፍት በልባቸው ውስጥ እንዲተከልና በእርሱም ተመሥርተው እንዲያድጉ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ የሆነበት ምክንያት የልብ ፍላጎት በብዙ ገጽታዎች ስለሚገለጥ ነው። ታዳጊዎችን ከፈተና ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እና ወደ ክርስቶስ ዘወር ካደረግናቸው ይህ የዲጂታል ዘመን ታዳጊ ልጆቻችንን ይበልጥ የምናስተምርበትንና ለደቀ መዝሙርነት የምናበቃበትን የተለያዩ ዕድሎችን ይዞ መጥቷል። ይህ እኛ ልናደርገው የሚገባ የወላጆች ፈተና ነው።  

የእኛ የወላጆች ቸልተኝነት በዲጂታል ዘመን ተጋልጧል። ይህንን ሐሳብ ከዚህ በላይ አላብራራውም፤ ምክንያቱም “12 ways that our phones change us” ብዬ በጻፍኩት መጽሐፍ ላይ በይበልጥ አንሥቼዋለሁ። በተጨማሪም ድርጊቶቻችን እና ንግግራችን እንዴት በመጽሐፍ ቅዱስ መቃኘት እንዳለበት በዚሁ መጽሐፌ ላይ አስቀምጫለሁ። እኛ ወላጆች (እና መጋቢዎች) የራሳችንን የዘመናዊ ስልክ አጠቃቀም ለመገምገም የሚያስፈልገውን ትሕትናን ካዳበርን ልጆቻችንን ደግሞ መርዳት እንችላለን። የዲጂታል ዘመን እጅግ አስፈሪ እና አድካሚ ነው። ነገር ግን በአግባቡ ከተጠቀምነው ታዳጊ ልጆቻንን እውነተኛ ደቀ መዝሙር ለማድረግ ብዙ አማራጮችን ይዟል።

11. እንደ ቤተሰብ፣ የራት ግብዣዎችን፣ የመኪና ጉዞዎችን እና የዕረፍት ጊዜዎችን ይዋጁ

የእራት ግብዣ፣ የመኪና ጉዞዎችን እንዲሁም የቤተሰብ የዕረፍት ጊዜዎችን ከስልክ ነጻ ያድርጉ። በእራት ጠረጴዛ ላይ የሕይወት ጫናዎች እንዴት ለማውራት እንደሚቀል ይገርመኛል። ያልተጣደፉ የአንድነት ጊዜያት እጅግ አስፈላጊ ናቸው። በትምህርት ቤት ምን ተፈጠረ? ስለ ልጆቼ ይበልጥ የማውቀው በእራት ሰዓት በምናሳልፈው ጊዜ ነው። ይህ የቤተሰብ ኅብረት በምንዝናናበት ጊዜም ይበልጥ ይጠናከራል።

12. ቤተ ክርስቲያንን መገንባት ቀጥሉ።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሜሪካ iGen 72 ዓመት ከሞላቸው የሕዝብ ክፍሎች ይልቅ ብቸኝነት የሚያጠቃው ትውልድ ነው። ትዌንግ እንደምታስረዳው የዚህ ብቸኝነት ምንጭ ደግሞ ዘመናዊ ስልኮች ናቸው። አይፎን ከመፈጠሩ በፊት የነበረውን ትላልቅ ክስተቶችን መመልከት ይህንን ለመረዳት አስፈላጊ ነው።

ራስዎን በበቂ ቴክኖሎጂ እና ማሽኖች ከከበቡ ሌላ ማንም አያስፈልጎትም። ትክክለኛውን መተግበርያ ካገኙ፣ ማንኛውንም ነገር ማድረግ ይችላሉ። ብዙ ሳይንሳዊ ልቦለዶች በሮቦት የተሞላችን ዓለም እንድትመሠረትና ማኅበራዊ መገለል እንዲስፋፋ ምክንያት ሆነዋል። ነገር ግን የቴክኖሎጂው ዘመን ሁሉም ሰው ለእናንተ አስፈላጊ እንዳልሆነ ካስገነዘባችሁ በኋላ፣ ለሌላው ሰው ደግሞ አስፈላጊ እንዳልሆናችሁ እንድትገነዘቡ ያደርጋል።

ማንም ሰው በማይፈልጋችሁ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ የብቸኝነት ስሜት ይሰማችኋል። የiGen ታዳጊዎች ይህ ይሰማቸዋል። ዕድሜያቸው ከፍ ያለውም ይህ ስሜት ይሰማቸዋል። ብቸኝነት እየጨመረ በሄደበት ዘመን፣ ማኅበራዊ ሚዲያ “መሠረት አልባ ለሆኑ በሽታዎች መሠረት የሌለው መድኀኒት ይሰጣል።” ዘመናዊ ስልክ የብቸኝነት ችግራችንን እንደሚፈታ ቃል በመግባት “የህመማችን ማስታገሻ” ይሆናል። ነገር ግን ህመሙ ተደበቀ እንጂ አልጠፋም። በሌላም ጊዜ ሊገለጥ ቀን እየጠበቀ ነው።

ዛሬ ታዳጊዎች የሚያስፈልጋቸው አዳዲስ እገዳዎች፣ ዘመናዊ ያልሆኑ ስልኮች እንዲሁም ኮንትራቶች ሳይሆን ትልቁ የሚያስፈልጋቸው ነገር በክርስቶስ ሆነው የሚያገለግሉት እና የሚገለገሉበት የእምነት ኅብረት ነው። እንደ ጤናማ የቤተ ክርስቲያን አካል አስፈላጊውን ቦታ ማግኘት አለባቸው። ታማኝ ቤተሰቦችን እና አብያተ ክርስቲያናትን ገንቡ። ታዳጊዎችን አድምጡ። አትሳለቁባቸው። በኢንተርኔት ላይ እንዲሁም ከኢንተርኔት ውጪ ለአደጋ በተጋለጡ ቦታዎች ላይ መልእክተኛ እንደሆኑ አስቡ።

ቶኒ ሬንክ