ለእግዚአብሔር ክብር የተኖረ ትዳር

ለዚህ ምዕራፍ ርዕስ እንዲሆን የመረጥኩት “ለእግዚአብሔር ክብር የተኖረ ትዳር” የሚል ዐረፍተ ነገር ነው። በዚህ ርዕስ ውስጥ ልናስተውለው የሚያስፈልገው ቃል “ለእግዚአብሔር” የሚለውን ነው። ርዕሱ “የእግዚአብሔር ክብር በትዳር ውስጥ” ወይም “በእግዚአብሔር ክብር የተኖረ ትዳር” ሳይሆን፣ ርዕሱ “ለእግዚአብሔር ክብር የተኖረ ትዳር” ነው።

ይህ አጭር ሐረግ፣ የቅደም ተከተል ተዋረድ እና የሆነ ግብ እንዳለው ያመለክታል። ቅደም ተከተሉም ግልጽ ነው፦ እግዚአብሔር የመጨረሻ ግብ ነው፤ ትዳር ግን አይደለም። እግዚአብሔር እጅግ አስፈላጊ የእውነታ መፍለቅያ ነው፤ ትዳር ግን ከዚህ እጅግ ያነሰ ነው። ትዳር የእግዚአብሔርን እውነት፣ ክብር፣ ውበትና ትልቅነት ለማጉላት የተፈጠረ እንጂ፣ እግዚአብሔር ትዳርን ለማጉላት አይኖርም። በዚህ ቅደም ተከተል መሠረት፣ ግልጽ በሆነ መልኩ እስካልተረዳነው እና እስካላከበርነው ድረስ ትዳር የእግዚአብሔር ክብር ተቀናቃኝ እንጂ የእግዚአብሔር ክብር የሚገለጥበት አይሆንም።

ትዳር ለምን ተፈጠረ?

”ለእግዚአብሔር ክብር የተኖረ ጋብቻ” የሚለውን ርዕስ የመረጥኩት፦ ትዳር ለምን ተፈጠረ? ለምን በትዳር ውስጥ እንኖራለን?  የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ነው። ይህ ርዕስ ከዚህ ሰፋ ያለ የሌላ ጥያቄ ክፍል ነው። ይህም ጥያቄ ማንኛውም ነገር ለምን ተፈጠረ? አንተስ/አንቺስ ለምንድን ነው የተፈጠርከው/ሺው? ለምንድን ነው የግብረ ሥጋ ግንኙነት የኖረው? ይህ ዓለም፣ ፀሓይና ጨረቃ የተፈጠሩት ለምንድን ነው? እንስሳቶች፣ ዕፅዋቶች፣ ውቂያኖሶች፣ ተራሮች፣ ጥቃቅን ንጥረ ነገሮች፣ አጽናፈ ዓለም እነዚህ ሁሉ የተፈጠሩት ለምንድን ነው? የእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልስ፣ የትዳርንም ጨምሮ፣ ሁሉም የተፈጠሩት ለእግዚአብሔር ክብር ነው የሚል ይሆናል።

ይህ ማለት የመኖራቸው ምክንያት የእግዚአብሔርን እውነት፣ ክብር፣ ውበት እና ታላቅነት ለማጉላት ነው። የሚያጎሉትም ማይክሮስኮፕ በሚያጎላበት መንገድ ሳይሆን፣ ቴሌስኮፕ በሚያጎላበት መንገድ ነው። ማይክሮስኮፕ ጥቃቅን ነገሮችን ትልቅ በማድረግ ሲያጎላ፣ ቴሌስኮፕ ግን እጅግ ትልቅ የሆኑትን ነገሮች ምን እንደሆኑ አቅርቦ ያሳየናል። ማይክሮስኮፕ ከእውነታ ዓለም በማራቅ የነገሮችን መጠን እጅግ አግዝፎ ሲያሳየን፣ ቴሌስኮፕ ግን ወደ እውነታው የመጠን ልክ ያደርሰናል። ሁሉም ነገሮች የእግዚአብሔርን እውነት፣ ክብር፣ ውበትና ትልቅነት እንዲያሳዩን ተፈጥረዋል ስል፣ ሁሉም ነገሮች (ትዳርን ጨምሮ) የሰዎችን አእምሮ ወደ እግዚአብሔር እውነተኛ የመገለጥ እውነታ እንዲመሩ ተፈጥረዋል ማለቴ ነው።

እግዚአብሔር ሊገመት በማይችል መልኩ እጅግ ውድ እና እጅግ ውብ ነው። “እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ እጅግ ሊመሰገንም ይገባዋል፤ ታላቅነቱም አይመረመርም” (መዝሙር 145፥3)። ወደ መኖር የመጣ የትኛውም ነገር ይህንን እውነት ለማላቅ የተፈጠረ ነው። እግዚአብሔር በነብዩ ኢሳይያስ አማካኝነት እንዲህ ይላል፦ “ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ፣ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፣ በስሜ የተጠራውን ሁሉ፣ ለክብሬ የፈጠርሁትን፣ ያበጀውትንና የሠራሁትን አምጡ” (ኢሳይያስ 43፥6-7)። የተፈጠርነው የእግዚአብሔርን ክብር ለማንጸባረቅ ነው። ጳውሎስ በታላቅ መልእክቱ፣ በሮሜ መጽሐፍ፣ የመጀመሪያዎቹን 11 ምዕራፎች ሲያጠቃልል የነገሮች ሁሉ ምንጭ እና ፍጻሜ እግዚአብሔርን በማላቅ እንደሆነ ይነግረናል፦ “ሁሉም ከእርሱ፣ በእርሱ፣ ለእርሱ ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን” (ሮሜ 11፥36)። በቆላስይስ 1፥16 ደግሞ ይህንን በይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል፦ “ሁሉ ነገር በእርሱ (በክርስቶስ) ተፈጥሮአል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት ቢሆኑ ኅይላት፣ ገዦች ቢሆኑ ባለሥልጣናት፣ ሁሉም ነገር በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል።”

ለእግዚአብሔር መፈጠር ማለት ምን ማለት ነው?

“ለእግዚአብሔር” ስንል “ለእርሱ ጥቅም” ወይም “ለእርሱ መኖር አስፈላጊነት” ወይም “ለእርሱ መሻሻል” ብለን ካሰብን ትልቅ ስሕተት ውስጥ እንገባለን። ጳውሎስ በሐዋሪያት ሥራ 17፥25 ይህንን ግልጽ በሆነ መልኩ እንዲህ ነግሮናል፦ “እርሱ ለሰዎች ሁሉ ሕይወትንና እስትንፋስን እንዲሁም ሌላውንም ነገር ሁሉ የሚሰጥ ስለሆነ፣ የሚጎድለው ነገር ባለመኖሩ በሰው እጅ አይገለገልም።” “ለክብሩ” እና “ለእግዚአብሔር” ማለት “ ለክብሩ ነጸብራቅ” ወይም “ክብሩን የሚያሳይበት” ወይም “ክብሩን ከፍ የሚያደርግበት” ማለታችን ነው።

ይህ ልናጤነውና ልናስተውለው የሚገባ ነገር ነው። እግዚአብሔር ብቻ የነበረበት ጊዜ ነበር። ዓለማት በእርሱ ተፈጠሩ እንጂ ከእርሱ ጋር የጋራ ሕልውና አልነበራቸውም፤ ወደ መኖር ያመጣቸው እርሱ ነው። “በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ሁሉ ነገር በእርሱ ተፍጥሮአል፤ ከተፈጠረው ሁሉ ያለ እርሱ የተፈጠረ ምንም የለም” (ዮሐንስ 1፥1-3)። ከራሱ ከእግዚአብሔር ውጪ ያለው ነገር ሁሉ የተፈጠረው በእርሱ ነው። በመጀመሪያ እግዚአብሔር ብቻ ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ፍጹም የሆነው እውነታ ነው። እኛ እንዲህ አይደለንም። አጽናፈ ዓለሙም እንዲህ አይደለም። ትዳርም አይደለም። እኛ ከእርሱ የመነጨን ነን። ይህ ዓለም ተከታይ እንጂ ቀዳሚ አይደለም። የሰው ዘር የመጨረሻ የእውነታ እና የዋጋ ልክ አይደለም። ሰውነት ፍጹም ትክክል የሆነውን፣ መልካም የሆነውን፣ ውብ የሆነውን የምንለካበት ሚዛናችን አይደለም። እርሱ እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር የመጨረሻው ፍጹም የሕልውና መገለጫ ነው። ሁሉም ነገር ከእርሱ፣ በእርሱ እና ለእርሱ ነው።

ስለ ትዳር ያለን ምልከታ ሊቀዳ የሚገባው ከዚህ መሠረታዊ እውነት ነው። ይህንን በተሳሳተ መንገድ ከተረዳነው ሁሉም ነገር ላይ እንሳሳታለን። ይህንን በትክክል በአእምሮአችን እና በልባችን ከተረዳነው ደግሞ ትዳራችን በዚህ እውነት ይለወጣል፤ ይታደሳልም። ትዳር በእግዚአብሔር ለተፈጠረለት ዓላማ ሲውል የእግዚአብሔርን እውነት፣ ክብር፣ ውበት እና ትልቅነት ይገልጣል።

ስለ ትዳር ስትሉ፣ እግዚአብሔርን ስበኩ!

ይህ በጣም ግልጽ ቢሆንም ረጅም ርቀት ወደሚያስኬድ ድምዳሜ ያደርሰናል። ጋብቻ በዚህ ዓለም እና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተገቢ ቦታ እንዲኖረው እና የእግዚአብሔርን እውነት፣ ክብር፣ ውበትንና ትልቅነት እንዲያጎላ ከፈለጋችሁ፣ ከትዳር የበለጠ ስለ እግዚአብሔር ስበኩ።

አብዛኞች ወጣቶች በእጮኝነት እና በትዳር ሕይወታቸው ውስጥ በእግዚአብሔር ማንነት፣ ባሕሪይ እና አሠራር ላይ ያጠነጠነ እይታ የላቸውም። በዚህ ዓለም ውስጥ እግዚአብሔርን ማወቅ የለም፤ እርሱን ማወቅም አይፈልጉም። እጅግ በሚያስገርም መልኩ እግዚአብሔር ተረስቷል። በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ ወጣት ጥንዶች አብረው ሲያሳልፉ የሚኖራቸው የእግዚአብሔር መረዳት ሰፊ ከመሆን ይልቅ እጅግ አናሳ፣ ግልጽ ከመሆን ይልቅ የደበዘዘ፣ ሁሉን አዋቂና በያኒ እንደሆነ ከመረዳት ይልቅ አቅመ ቢስ ይሆናል። ከዚህም የተነሣ ጥንዶች ወደ ትዳር ሲመጡ፣ “ለእግዚአብሔር ክብር ትዳርን መኖር” የሚለው ሐሳብ ትርጉም እና እርካታ የሌለው ነገር ይመስላቸዋል።

የእግዚአብሔር ክብር ስንል ምን ማለታችን ነው?

የእግዚአብሔርን ክብር ወይም የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር ለማወቅ ጊዜ ለማይሰጡ፣ ደግሞም ስለ ጉዳዩ የጠለቀ መረዳት ለሌላቸው ወጣት ጥንዶች፣ “የእግዚአብሔር ክብር” ምን ማለት ነው?

  • የዘላለማዊነቱ ክብር፦ ጅማሬ በሌለው እና ሁሌም በሚኖረው አምላክ፣ አእምሯችንን በማያልቁ ድንቅ ሐሳቦች የሚቆጣጠር
  • የዕውቀቱ ክብር፦ በዓለማችን ታላቅ የሚባለውን ቤተ መጽሐፍት እንደ ኢምንት የሚያስቆጥር
  • የጥበቡ ክብር፦ የሰው ልጅ ሊመክረው የማይችል
  • የሥልጣኑ ክብር፦ በሰማይ፣ በምድርና ከምድርም በታች ከእርሱ ፈቅድ ውጪ አጋንንት እንኳ ቢሆን ምንም ሊያደርግ የማይችል
  • የመግቦቱ ክብር፦ ከእርሱ መግቦት ውጪ አንድ ቅጠል እንኳ መሬት መውረድ የማይችል፣ አንዲት ጸጉር ያለ እርሱ ፈቃድ የማይሸብት
  • የቃሉ ክብር፦ ዓለማትን ቢሆን ጥቃቅን ንጥረ ነገሮችን ደግፎ የያዘ
  • የኃይሉ ክብር፦ በውሃ ላይ የሚራመድ፣ ለምጻሞችን የሚያነጻ፣ ሽባዎችን የሚፈውስ፣ የዕውሮችን ዐይን የሚያበራ፣ ደንቆሮዎችን የሚፈውስ፣ በቃሉ ወጀብን ዝም የሚያሰኝ፣ ሙታንን የሚያስነሣ
  • የንጽሕናው ክብር፦ ኃጢአትን ፈጽሞ ሊሠራ የማይችል፣ ክፉን ፈጽሞ ሊያስብ የማይችል
  • የታማኝነቱ ክብር፦ ቃሉን ፈጽሞ ሊያጥፍ የማይችል
  • የፍርዱ ክብር፦ በአጽናፈ ዓለም ላይ ያሉትን ሁሉንም ድርጊቶች በተመለከተ በመስቀሉ ወይም በሲኦል ፍትሕን የሚያሰፍን
  • የትዕግስቱ ክብር፦ በዓመታት መካከል ድንዛዜያችንን የታገሰበት የትዕግስት ልክ
  • የሉዓላዊነቱ ክብር፦ በሕመም የተሞላውን የመስቀሉን ሥቃይ ለመቀበል እንደ ባሪያ መታዘዙ 
  • የቁጣው ክብር፦ አንድ ቀን ሁሉም ሰዎች ድንጋዮችና ተራሮች እንዲወድቅባቸው እስከሚጠሩ ድረስ የቁጣው አስፈሪነት
  • የጸጋው ክብር፦ ኃጢአተኛውን የሚያጸድቅ
  • የፍቅሩ ክብር፦ ኃጢአተኞች ሳለን የሞተልን

ሰዎች ይህንን እውነት ለማወቅ የማይፈልጉ እና ጊዜ የማይሰጡ ከሆነ፣ ታዲያ ትዳር የእግዚአብሔርን ክብር፣ ዋጋ፣ እውነት፣ ውበት እና ትልቅነት እንዴት ያሳያል?

የሕይወቴ እና የቤተ ክርስቲያናችን ተልእኮ

ባለፉት 20 ዓመታት በነበረኝ የእረኝነት አገልግሎት ውስጥ፣ የቤተ ክርስቲያናችን እንዲሁም የእኔ የግል ሕይወት ትልዕኮ እንዲህ ነው፦ እኛ የተፈጠርነው፣ እኔ የተፈጠርኩት እና የምኖረው፣ እግዚአብሔር በሁሉም ነገሮች ላይ ያለውን ታላቅነትና ልዕልና በመስበክ ለሕዝቦች ሁሉ ደስታን ለማምጣት ነው። በተጋቡ ጥንዶች መካከል፣ የእግዚአብሔርን ክብርና ልዕልና ለሰዎች ለማብሰር የተዘጋጀ ልብ ከሌለ ጋብቻ ለእግዚአብሔር ክብር ሊኖር አይችልም።

ጥንዶች እግዚአብሔር ራሱን ካላወቁ፣ ለእግዚአብሔር ክብርና ልዕልናን ቦታ አይኖራቸውም። መጋቢዎችም ሳይታክቱ ሁልጊዜ በትጋትና ለመጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ ሆነው እግዚአብሔርን ካልሰበኩ፣ እግዚአብሔር በሕዝቡ ሊታወቅ አይችልም። ለእግዚአብሔር ክብር የተኖረ ትዳር፣ ለእግዚአብሔር ክብር የቆመ ቤተ ክርስቲያን ነጸብራቅ ነው።

ይህንን ደግሜ እላለሁ፦ ትዳር የእግዚአብሔርን ታላቅነት፣ ክብር፣ ውበት እና እውነት ከፍ አድርጎ እንዲያሳይ ከፈለግን፣ ከትዳር ይልቅ ስለ እግዚአብሔር መስበክና ማስተማር አለብን። ከእግዚአብሔር ይልቅ ስለ ትዳር መስበክ የለብንም። እግዚአብሔር በብዙ ሰዎች ዘንድ የሕይወታቸው ዋና ማዕከል አይደለም። በሕይወታቸው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ውስጥ ፕላኔቶች በዛቢያቸው የሚዞሩበት ፀሓይ እግዚአብሔር አይደለም። እግዚአብሔር ለአብዛኞች እየደከመና እየከሰመ እንደሚመጣ እንደ ጨረቃ ነው፤ ስለ እርሱም ምንም ሳታስቡ ብዙ ሌሊቶችን ልታሳልፉ ትችላላችሁ።

በቤተ ክርስቲያን ያሉ አብዛኞቹ ምዕመናን፣ የተለያዩ ነገሮች የእግዚአብሔርን ቦታ ተናጥቀውባቸዋል። የእጮኝነትን ትምህርት ያለ እግዚአብሔር ማዕከላዊነት ማስተማር ማለት፣ ቴሌስኮፕ ሳይገዙ እና ምሽት ላይ ወደ ሰማይ ሳያዩ፣ ጨረቃን አጉልቶ ለማየት እንደመጣር ነው።

በትዳር ውስጥ እንዴት ለእግዚአብሔር ክብር መኖር ይቻላል?

እግዚአብሔርን ከሁሉ ነገር (ትዳር አጋራችንን ጨምሮ) ይልቅ ዋጋ መስጠትና ማክበር፣ ጋብቻን ለእግዚአብሔር ክብር እንድንኖር የሚያደርግ እጅግ አስፈላጊ መረዳት ነው። በትዳርም ሆነ በየትኛውም ግንኙነት እውነት እንደሆነው ሁሉ፣ እግዚአብሔር በእኛ እጅግ የሚከብረው በዋነኝነት በእርሱ እርካታን ያገኘን እንደሆነ ነው።

ለሺህ በሮች መክፈጫ ቁልፍ ይህ ነው። ከምድራዊ ነገሮች ሁሉ፣ ከትዳር፣ ከጤንነት እንዲሁም ከራሳችን ሕይወት ይልቅ (ዘማሪው “ምሕረትህ ከሕይወት ይበልጣልና” እንዳለው፣ መዝሙር 63፥3) በእግዚአብሔር ላይ ያለን የላቀ እርካታ፣ በክርስትና ሕይወት መክፈል ላለብን ዋጋ ሁሉ የአቅም ምንጭ ነው። ይህ ካልሆነ ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደ ክርስቶስ ሊወዱ፣ ሚስቶችም እንደ ክርስቶስ ሙሽራ ባሎቻቸውን ሊከተሉ አይችሉም። ኤፌሶን 5፥22-25 ግልጽ እንደሚያደርገው ባሎች የመምራት እና የመውደድ ኅላፊነታቸውን ከክርስቶስ ሲማሩ፣ ሚስቶች ደግሞ የመገዛት እና የመውደድ ኅላፊነታቸውን ቤተ ክርስቲያን ለሞተላት ለክርስቶስ እንዲያደርጉ ያስተምራል። እነዚህ በተጓዳኝነት የሚሄዱ የመምራት እና የመገዛት የፍቅር ድርጊቶች፣ እግዚአብሔር በክርስቶስ ባደረገልን ካልረካን ቋሚና የሚጸኑ አይሆኑም።

እግዚአብሔር በጋብቻ ክብሩን የሚያበራበት ሁለቱ መንገዶች

በሌላ መንገድ ሳስቀምጠው፣ እግዚአብሔር ክብሩን በክርስቲያን ጋብቻ የሚገልጽበት ሁለት እርከኖች አሉ።

አንደኛው፣ በመዋቅራዊ ደረጃ ሲሆን ይህም ሁለቱም የትዳር አጋሮች እግዚአብሔር የሰጣቸውን ኅላፊነት ሲወጡ ነው። ይህም ባል ክርስቶስን በመምሰል ሲመራ፣ ሚስትም ስትገዛ ነው። እነዚህ ኅላፊነቶች በአግባቡ ሲፈጸሙ እግዚአብሔር በክርስቶስ የገለጠው ፍቅሩ እና ጥበቡ ለዓለም ይታያል።

በተጨማሪ ደግሞ ዋነኛው ነገር፣ እነዚህ ኅላፊነቶች እግዚአብሔር ባስቀመጠው መንገድ ሲፈጸሙና የእግዚአብሔር ክብር ሲበራ ነው። ፍጹም ያልሆነችን ሚስት ለመውደድ፣ ፍጹም ያልሆነን ባል ለመውደድ የሚጠይቀው ራስን በየዕለቱ፣ በየወሩ፣ የየዓመቱ መካድ ነው፤ ይህም የመካድ ኅይል የሚመነጨው፣ በእግዚአብሔር ላይ ካለን ተስፋ እና በእርሱ ውስጥ ከምናገኘው፣ ነፍስን ከሚያሳርፍ የላቀ እርካታ ነው። ከትዳራችን በላይ በእግዚአብሔር ካልተደሰትን ለሚስቶቻችን ያለን ፍቅር ወይም እነርሱ ለእኛ ያላቸው ፍቅር ለእግዚአብሔር ክብር የሚያመጣ አይመስለኝም።  

ጋብቻ ለእግዚአብሔር ክብር የሚጠበቀውና ለእርሱ ክብር ብቻ የሚውለው፣ የእግዚአብሔር ክብር ከትዳራችን በላይ በእኛ ዘንድ የከበረ ሲሆን ነው። ለባላችን ወይም ለሚስታችን፣ እንደ ጳውሎስ “ወደር የሌለውን ጌታዬን ክርስቶስ ኢየሱስን ከማወቅ ታላቅነት ጋር ሳነጻጽር፣ ሁሉንም ነገር እንደጉድለት እቆጥረዋለው” ማለት ስንችል ጋብቻ ለእግዚአብሔር ክብር ተኖረ ማለት እንችላለን (ፊልጵስዮስ 3፥8)።

ጆን ፓይፐር