እውነተኛ ደስታ ከወሲብ ኀጢአት ነፃ አወጣው

አውግስጢኖስ (354-430)

አውግስጢኖስ በምዕራቡ ዓለም ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ እጅግ ከፍተኛ ነው።

ቤንጃሚን ዋርፊልድ እንደሚናገረው፣ አውግስጢኖስ በጽሑፉ ውስጥ ወደ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ወደ ዓለም እንደ አብዮተኛ ኅይል ነበር የገባው። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ አንድን ምዕራፍ ብቻ ሳይሆን የፈጠረው፣ እስከዛሬ ድረስ በምዕራቡ ዓለም የሚታየውን የታሪክ አቅጣጫ ነበር ያቀናው (ካልቪን እና አውግስጢኖስ፣ ገጽ 306)። የክርስትና ታሪክ የተሰኘው መጽሔት አሳታሚዎች እንዳሉት “ከኢየሱስ እና ጳውሎስ በመቀጠል በክርስትና ታሪክ ውስጥ ታላቅ ተፅዕኖ ካላቸው ስመጥር ሰዎች መካከል አውግስጢኖስ በዋነኛነት ይጠቀሳል።”

የርካሽ ፍቅሮች መፍያ አፍላል

አውግስጢኖስ የተወለደው እ.ኤ.አ. ሕዳር 13፣ 354 አሁን ላይ አልጄሪያ በመባል በምትታወቀው ታጋስቴ የምትባል ስፍራ ነበር። ታጋስቴ ሂፖ በምትባለው ከተማ አቅራቢያ ያለች ከተማ ነች። መካከለኛ ገቢ የነበረውና በግብርና ሥራ ይተዳደር የነበረው አባቱ ፓትሪሺየስ፣ ልጃቸው አውግስጢኖስ በንግግር ጥበብ ሊያገኝ የሚችለውን የላቀ ትምህርት ሁሉ እንዲያገኝ ጠንክረው ይሠሩ ነበር። ዕድሜው ከዐሥራ አንድ እስከ ዐሥራ አምስት አመት ሳለ ከሚኖርበት ስፍራ ሠላሳ ሁለት ኪሎ ሜትር የሚያክል ርቃ በምትገኝ ማዳውራ የተባለች ከተማ ተማረ። በመቀጠልም አንድ ዓመት ቤት ወስጥ ከቆየ በኋላ ከዐሥራ ሰባት ዓመቱ አንሥቶ ሀያ ዓመት እስኪሞላው በካርቴጅ ትምህርቱን ተከታተለ።

አውግስጢኖስ ለሦስት ዓመት ትምህርት ወደ ካርቴጅ ከመሄዱ በፊት እናቱ ዝሙት እንዳይፈጽም ከምንም በላይ ደግሞ የማንንም ሚስት እንዳያማልል አበክራ አስጠንቅቃው ነበር። ይሁን እንጂ አውግስጢኖስ ከጊዜ በኋላ ኑዛዜ በተሰኘ መጽሐፉ ላይ እንዳሰፈረው “የርካሽ ፍቅሮች መፍለቅለቂያና መፍያ አፍላል ወደ ሆነው ካርቴጅ መጣሁ… በውስጤ ውስጣዊ ምግብ የሆንከው የአንተ የአምላኬ የማያቋርጥ ርኀብ ነበር።”[1] በካርቴጅ አንድ እቁባት ይዞ ለዐሥራ አምስት ዓመት አብሯት የኖረ ሲሆን አዲዎዳቱሰ የተባለ አንድ ወንድ ልጅ ከእርሷ ወልዷል።

አውግስጢኖስ ከዐሥራ ዘጠኝ ዓመቱ አንሥቶ እስከ ሠላሳ ዓመቱ ድረስ ለሚቀጥሉት ዐሥራ አንድ ዓመታት የንግግር ጥበብ መምህር በመሆን ያስተምር ነበር።

ከአምብሮስ ጋር በሚላን

29 ዓመቱ ሲሆን ሊያስተምር ከካርቴጅ ተነሥቶ ወደ ሮም ሄደ። ይሁን እንጂ በተማሪዎቹ ባሕሪ ስለተሰላቸ ሚላን ውስጥ ወደሚገኝ ማስተማሪያ ጣቢያ በ384 እ.ኤ.አ. ተዘዋወረ። በዚያ ሳለ ከታላቁ ጳጳስ አምብሮስ ጋር ተገናኘ።

በወቅቱ የፕሌቶን ሥነ ፍጥረት ሲጋት ስለነበረ፣ አውግስጢኖስ “ቃልም ሥጋ ሆነ” (ዮሐንስ 1፥14) በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እጅጉኑ ተደናገጠ። ይሁን እንጂ ከሳምንት እስከ ሳምንት አምብሮስ ሲሰብክ ይሰማ ነበር። “እንዴት በጥበብ እንደሚናገር ልቦናዬን ከፍቼ ሳደምጠው ምን ዓይነት እውነትም እንደሚያወራ ተገነዘብኩ” (ኑዛዜ፣ ገጽ 111)። መጨረሻም አውግስጢኖስን ወደኋላ የያዘው፣ የማሰብና የመረዳት ጉዳይ ሳይሆን የወሲብ ፍላጎት እንደሆነ ተረዳ። “ይሁን እንጂ በሴቶች ፍቅር እጅግ እንደተሳብኩ ነበርኩኝ” (ኑዛዜ፣ ገጽ 172) ።

ስለዚህ ውጊያው የሚዳኘው በሕይወቱ ውስጥ እያየለ ባለው የፍስሐ ዓይነት ሆነ። “በአንተ ደስ እንድሰኝ ጥንካሬ እንዲኖረኝ የሚያስችሉኝን መንገዶች ለማግኘት መፈለግን ጀመርኩኝ። ነገር ግን በእግዚአብሔር እና በሰዎች መካከል ያለውን መካከለኛ አገናኝ ኢየሱስ ክርስቶስን… እስካቅፍ ድረስ እነዚህን መንገዶች ማግኘት አልቻልኩም ነበር” (ኑዛዜ፣ ገጽ 164)።

ጽኑ ፍልሚያ 

በመቀጠል በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ወሳኝ ከሚባሉ ቀኖች ውስጥ አንዱ ተከሰተ። ይህ ታሪክ ኑዛዜ የሚለው መጽሐፉ የልብ ትርታ ነው። በታሪክ ውስጥም ከምንመለከታቸው ታላቅ የጸጋ ሥራዎች ውስጥ አንዱ ነው። እንዴት ያለ ፍልሚያ ነበር!

ይህ ቀን ብዙ ጊዜ ከሚተረክበት መንገድ የበለጠ የተወሳሰበ ቢሆንም፣ የፍልሚያው ማዕከላዊ ሐሳብ ጋር ለመድረስ ግን የመጨረሻው ቀውስ ላይ እናተኩር። ወቅቱ ነሐሴ መጨረሻ እ.ኤ.አ. 386 ዓ.ም. ነበር። የአውግስጢኖስ ዕድሜ ወደ 32 እየተጠጋ ነበር። ከቅርብ ጓደኛው አሊፒየስ ጋር ስለ ግብጻዊው መነኩሴ አንቶኒ ታላቅ መሥዋዕትነት እና ቅድስና እያወሩ ነበር። ሌሎች ሰዎች በክርስቶስ ነፃ እና ቅዱስ ሆነው ሲኖሩ እርሱ ግን በሴሰኝነት ተጠምዶ እየኖረ መሆኑ ወቀሰው።

“አርፈንበት ከነበረው ቤት አጠገብ ትንሽ መናፈሻ ነበረች።… ወደዚያ ስፍራ በውስጤ ጩኸት ተገፋፍቼ ፈጠንኩ። ከራሴ ጋር ከገባሁበት የተፋፋመ ፍልሚያ እልባቱ ምን ሊሆን እንደሚችል፣ ጌታ ሆይ እኔ ሳልሆን አንተ ነህ የምታውቀው። እዚያም ሆኜ ማንም ሊያስተጓጉለኝ አይችልም። ጤንነቴ እንዲመለስልኝ እንደ እብደት እያደረገኝ ሕይወትን የሚሰጥን ሞትን እየሞትኩ ነበር።… መንፈሴ ሰላም ነስቶኝ ነበር። የአንተን ፈቃድ ባለመቀበሌና ወደ አንተ ቃል ኪዳን ባለመግባቴ፣ በራሴ የራሴው ንዴት አቅሌን ነስቶኛል… እንደዚሁ ሁሉ ጸጉሬን ነጨሁ፤ ግንባሬን ኮማተረኩ፤ ጣቶቼን ቆላለፍኩ ጉልበቴን ጸፋኹ” (ኑዛዜ፣ ገጽ 188-189)።

ነገር ግን ካጣው ይልቅ የሚያገኘው የላቀ እንደሆነ የበለጠ ማየት ጀመረ። በጸጋውም ተአምር በክርስቶስ መገኘት ዘንድ ታቅቦ የመኖርን ውበት መረዳት ጀመረ።

“ዋነኛው የጊዜ ማሳለፊያ አሳለፊ የከንቱዎችም ከንቱ የሆንኩት ሰው የጥንት እመቤቶቼ አሁንም ይሳቡኝ!… ሥጋዊ ልብሴን እየጎተቱና በለሆሳስ እያንሾካሾኩ “ከእኛ ልትለይ ነው?” ከተለየኸን ቅፅበት ጀምሮ እስከ ዘላለሙ መቼም አንገናኝም ማለት ነው?… ፊቴን ወዳቀናሁበት ወደዚያ ለመጓዝ ብንቀጠቀጥም ራስን የመግዛት የንጽሕና ክብር እየታየችኝ ታበረታኝ ነበር። ዘናም ባልል ምን እሆን ብዬ ሳልጨነቅ በታማኝነት ያለ ምንም ጥርጣሬ እንድቀርባት ሳበችኝ። እጅግ ብዙ ብዙም በሆኑ መልካም አብነቶች የተሞሉ የተቀደሱ እጆቿን ዘረጋችልኝ” (ኑዛዜ፣ ገጽ 194-195)።

አንሣና አንብብ!

ስለዚህ ፍልሚያው ሥጋውን ይነጩት ከነበሩት እና የንጽሕና ክብር ከጣፋጭ ፍቅሯ ጋር ሆነ።

“ከሆነ የበለስ ዛፍ ሥር ተደፍቼ ዕንባዬን አነባሁ. . . እነዚህን የሐዘን ቃላት ወደ ላይ ከፍ ከፍ አደረግሁ እስከ መቼ እስከ መቼ? ነገ እና ነገ? ለምን አሁን አይሆንም? የአሁኗ ሰዓት ለምን የርኩሰቴ ፍጻሜ አትሆንም? “(ኑዛዜ፣ ገጽ 196)

በለቅሶም መሀል አውግስጢኖስ አንድ ሕጻን ልጅ “አንሣና አንብብ! አንሣና አንብብ!” እያለ ሲዘምር ሰማ።

“ወዲያው ራሴን መግዛት አቃተኝ ልጆች በየትኛው ጨዋታ እንደዚህ ዓይነት ቃላት ሊናገሩ እንደሚችሉ በማሰብ ተወጠርኩ ወይም ከዚህ በፊት ይህንን የሚመስል ሰምቼ እንደሆን ለማስታወስም አልቻልኩም። ስለዚህ የእንባዬን ጎርፍ ፈትቼ ተነሣሁ። ሌላ ምንም ሳይሆን ለእኔ ከሰማይ መጽሐፉን እንድከፍት የመጣ ድምጽ ነው ብዬ በመውሰድ የማገኘውንም የመጀመሪያ ምዕራፍ ማንበብ አለብኝ በማለት ተነሣሁ” (ኑዛዜ፣ ገጽ 197)።

ስለዚህ አውግስጢኖስ የጳውሎስ መልእክት መጽሐፉን አነሣና ከፈተው። ዓይኖቹ በሮሜ 13፥13-14 ላይ አረፉ፦ “በጭፈራና በስካር አይሁን፤ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፤ በክርክርና በቅናትም አይሁን። ይልቁንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም ይፈጽም ዘንድ ለሥጋ በዐሳባችሁ አትመቻቹለት።”

“ከዚያ በላይ አላነበብኩም፤ ማንበብም አላስፈለገኝም” በማለት ይጽፋል። “እነዚያ ዐረፍተ ነገሮች እንዳለቁ በቅጽበት እንደ ብርሀን ጮራ በልቤ ውስጥ የእፎይታ እርጋታ ሰፈነ። ያ ሁሉ የጥርጣሬ ጭጋግ በኖ ጠፋ” (ኑዛዜ፣ ገጽ 197)።

የሂፖ ጳጳስ

ቀጣዩ የትንሣኤ በዓል ላይ በ387 ዓ.ም. እ.ኤ.አ. ሚላን ከተማ ውስጥ አምብሮስ አጠመቀው። በዚያው መኸር ወቅት እናቱ ሞተች። የዕንባ ልጇ በክርስቶስ አስተማማኝ ጥበቃ ውስጥ ስለነበረ ደስተኛ ሆና ነበር የሞተችው። በ388 ዓ.ም. እ.ኤ.አ. ወደ አፍሪካ ተመለሰ (34 ዓመቱ ሊሞላው አካባቢ)። ዓላማውም የእግዚአብሔር አገልጋዮች ብሎ ለሚጠራቸው ለእርሱ እና ጓደኞቹ ገዳም መሰል ነገር ሊመሠርት በማሰብ ነበር። የማግባት ዓላማውን በመተው በብሕትውና እና በድህነት ለመኖር ራሱን ሰጠ። ይህም በማሕበረሰብ ውስጥ ከሌሎች ጋር የሚጋራውን የሕይወት ዘይቤ መተው ነው። በገዳማዊ ጉዞ የፍልስፍና ማሰላሰል ሕይወት እንደሚኖረው ተስፋ አድርጎ ነበር።

ነገር ግን እግዚአብሔር ሌላ ዕቅድ ነበረው። በ389 ዓ.ም. እ.ኤ.አ. የአውግስጢኖስ ልጅ አዲዎዳቱሰ ሞተ። ወደሚኖርበት ታጋስቴ ከተማ ተመልሶ ጸጥ ያለ ሕይወት የመምራት ሕልሙ በዘላለም ጥላ ሥር ተነነ። አውግስጢኖስም ከገዳማዊ ማሕበሩ ተለቅ ወደምትለው ሂፖ ወደተባለችው ከተማ ማዘዋወር የተሻለ ሳይሆን አይቀርም ብሎ አሰበ። የሂፖ ከተማ በጊዜው ጳጳስ ስለነበራት ጳጳስ ሁን ብለው አይጫኑኝም በሎ በማሰብ ነበር የመረጣት። ይሁን እንጂ ስሌቱ ልክ አልነበረም። ቤተ ክርስቲያኒቱ ወደ እርሱ መጥታ ቄስ እንዲሆን በኋላም የሂፖ ጳጳስ እንዲሆን አስገደደችው። እስኪሞት ድረስ የቆየው በዚያው ነበር።

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የጸና ምልክታቸውን እንዳኖሩ ብዙዎች ከማሰላሰል ሕይወት ወደ ድርጊት ሕይወት ተገፋፉ (በ66 ዓመቱ)። አውግስጢኖስ በቤተ ክርስቲያን መሠረት ላይ ገዳምን አቋቋመ። 40 ለሚሆኑ ዓመታት በአሕጉሩ ዙሪያ የተሾሙና ለቤተ ክርስቲያን ተሐድሶን ያመጡ በመጽሐፍ ቅዱስ የረሰረሱ ቄሶችን እና ጳጳሳትን አፈራ። ይህንን እያደረገ ለትክክለኛው የክርስትና አስተምህሮ ዘብ በመቆም በክርስትና ታሪክ ውስጥ ስመ ጥር ከሆኑ መጽሐፍት ውስጥ የተወሰኑትን ጽፏል። ከእነዚህም ውስጥ “ኑዛዜን” ጨምሮ፣ “የክርስትና አስተምህሮ”፣ “ሥላሴ” እንዲሁም “የእግዚአብሔር ከተማ” የሚሉት ይጠቀሳሉ።

ከመሞቱ አራት ዓመት በፊት በ426 ዓ.ም. እ.ኤ.አ. አውግስጢኖስ የማስተዳደር ሥልጣኑን ሲያስረክብ፣ ተተኪው በብቃት ማነስ ስሜት ተሞልቶ ነበር። የዚህ ታላቅ መንፈሳዊ ሰው ድምጽ በጊዜ ውስጥ ይጠፋል ብሎ በመሥጋት “ዳክዬው ጸጥ ብሏል” አለ።

ይሁን እንጂ ዳክዬው ጸጥ አላለም። በ426 ዓ.ም ጸጥ አላለም፣ አሁን በዘመናችን ጸጥ አላለም፣ እንዲሁም በመካከል በነበሩት ክፍለ ዘመናት ሁሉ ጸጥ አላለም። የአውግስጢኖስ ድምጽ ለ1,600 ዓመታት ረሀብተኛ ኃጢአተኞች ነፃ የሚያወጣውን የኢየሱስ ክርስቶስን ሉዓላዊ ደስታ እንዲመገቡ መጋበዝ ቀጥሏል።

“ከከንቱዎቹ ደስታዎች ውጭ መሆኔ ምነኛ ጣፈጠኝ! ያን በአንድ ወቅት እንዳላጣው የፈራሁት መገለሌ፣ ዛሬ ደስታዬ ሆኗል። አንተ እውነተኛና እጅግ የጣፈጥክ ከእኔ አውጥተህ ጥለህልኛልና።  አንተ እነርሱን አውጥተህ ጥለሀል። በእሾሆቹም ምትክ አንተ በራስህ ገብተሀል። ምንም ሥጋና ደም ባትሆን ከደስታዎች ሁሉ በላይ የጣፈጥክ ከብርሀን ሁሉ በላይ ብርሀን የሆንክ፣ ነገር ግን ከተሰወሩት ሁሉ በላይ የተሸሸግህ፣ ከክብሮች ሁሉ በላይ የከበርክ በሆንከው ባንተ እንጂ የከበሩት በራሳቸው ትምክህት አይደለም።… ብርሃኔ፣ ሀብቴ፣ ጤናዬ፣ ጌታዬም አምላኬ እልሃለሁ” (ኑዛዜ፣ ገጽ 199-200)።

ጆን ፓይፐር


[1] ዘካሪያስ ደበበ፤ ቅዱስ አውግስጢኖስ፣ ኑዛዜ፣ (ጥበብ የምርምርና የጽሞና ማእከል፣ 2013 ዓ.ም.)