ጳውሎስ፣ “ግራ ብንጋባም ተስፋ አንቈርጥም” በማለት አክሏል። ግራ መጋባት ብዙውን ጊዜ ከመከራ ጋራ ዐብሮ ይመጣል። በሕመም ወይም በሐዘን ስንመታ፣ ብዙውን ጊዜ ግራ እንጋባለን፤ እንዲሁም ይምታታብናል። የመጀመሪያ ጥያቄያችን “ለምን?” የሚል ነው። “ይህ እንዲደርስብኝ እግዚአብሔር እንዴት ይፈቅዳል?” በማለት እንጠይቃለን።
በልጁ ሞት እጅግ ዐዝኖ የነበረ፣ አንድ የተጨነቀ አባት ታሪክ ትዝ ይለኛል። ወደ መጋቢው ይሄድና ግራ በተጋባ ንዴት፣ “ልጄ ሲሞት እግዚአብሔር የት ነበር?” ብሎ ይጠይቀዋል። መጋቢውም በተረጋጋ መንፈስ፣ “ልጁ ሲሞት በነበረበት ተመሳሳይ ቦታ” በማለት ይመልስለታል።
ከመከራ ጋር የተያያዘ የሆነ የመደነቅ ነገር አለ። ሥቃዩ የሕይወት ክፍል መሆኑን ቀደም ብለን እንማራለን፤ ነገር ግን የመማር ሂደቱ አብዛኛውን ጊዜ ቀስ በቀስ የሚቀጥል ነው። የሦስት ዓመት የልጅ ልጄ ሕመምን የሚቋቋምበት መንገድ ያዝናናኛል። አንድ ነገር ሲጐዳው፣ “አባባ፤ ‘አውች’ አለብኝ” በማለት ይናገራል። አውች የሚለውን ቃል እንደ ስም ይጠቀመዋል። የእርሱ “አውች” ቀላል ከሆነ፣ በመሳም ብቻ ማባበል ይቻላል። ይበልጥ ከባድ ከሆነ ደግሞ፣ የቁስል ፕላስተር ይጠይቃል።
አብዛኞቹ የልጅነት ሕመሞችና ቊስሎች ቀላል ናቸው። አንድ ሕፃን የሆድ ቫይረስ ሲይዘው፣ ስለ ካንሰር አይጨነቅም። የልጅነት ሕመሙ የሚያስከትለው ሥቃይ በቅርቡ እንደሚወገድ በፍጥነት ይገነዘባል። ይሁን እንጂ፣ እንደ ዐዋቂዎች፣ ወደ ሌላ የበሽታና የሥቃይ ደረጃ እንሸጋገራለን። ምንም እንኳ በዝግጅት ደረጃዎች ውስጥ ብንጓዝም፣ ከበድ ባለ በሽታ ስንጠቃ ፈጽሞ ዝግጁዎች አይደለንም።
ልጄ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሆስፒታል ስትሄድ ትዝ ይለኛል። የስድስት ዓመት ልጅ የነበረች ሲሆን እንጥሏን ማስወገድ ነበረባት። እንደ ወላጆች፣ እርሷን ለማዘጋጀትና ከሚመጣው ነገር ለመከላከል ሁሉንም ርምጃዎች ወስደናል። ወደ ሆስፒታል ስለ መሄድ የሚናገሩትን የልጆች መጻሕፍት እናነብላት ነበር። ከቀዶ ሕክምናው በኋላ የምትወድደውን አይስክሬም እንደምንሰጣት አረጋገጥንላት።
ወደ ሆስፒታሉ ያደረግነው ጒዞ እንደ አዲስ የሚያስደስት ተመክሮ ነበር። የሆስፒታሉ የሕፃናት ክፍል በደማቅ ሁኔታ አጊጦ ነበር። ነርሶቹ ልጃችንንና ጓደኛዋን በአሻንጉሊት አዝናኗቸው። መንፈሷ ከፍ ብሎ፣ ፍርሀቷ ደግሞ ዝቅ ብሎ ነበር።
ወደ ቀዶ ሕክምና ክፍል ከተወሰዱ በኋላ፣ ከማገገሚያው ክፍል እስኪመለሱ መጠባበቅ ጀመርን። ልጄ ከነቃች በኋላ ያየችኝን ዕይታ መቼም አልረሳውም። አሳዛኝ ዕይታ ነበር። የደረቀው ደም በከንፈሮቿ ጫፍ ተጋግሮ ነበር። ፊቷ ገርጥቷል። ይሁን እንጂ በጣም የሚረብሸው ነገር ፍርሀቷ፣ ድንጋጤዋና የመከዳት ስሜቷ ነው። በአዲስ የሥቃይ ምዕራፍ እያለፈች ነበር። በዐይኖቿ እንዲህ እያለችኝ እንዳለ ያህል ተሰማኝ፣ “እንዴት ይህን ታደርጋለህ? እንዲህ እንደሚሆን ታውቅ ነበር እናም ዋሸኸኝ።” በዚያ ሰዓት ምንም ግድ ያልሰጣት ነገር ቢኖር አይስክሬሙ ነበር። በሥቃይዋ ተደንቃ ነበር፤ እንደ ጠበቀችው አልነበረምና።
ይህ ክፍለ ምንባብ ተስፋ ሳይቈርጡ ግራ መጋባት እንዴት እንደሚቻል ያሳያል። መከራችን ዐላማ አለው።
ድንገተኛ ሥቃይ ሲደርስብን በሰማይ ስላለው አባታችን የምንጠይቃቸው ተመሳሳይ ጥያቄዎች ዐይነት፣ ልጄም በእኔ ላይ እንደ ነበረባት ርግጠኛ ነኝ። ልክ እንደ ልጄ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ያለ ከባድ መከራ እንዲደርስብን መፍቀዱ ብዙ ጊዜ ያስደንቀናል። መደነቁ የሚመነጨው፣ እግዚአብሔር እንድናምን ከሚመራን ነገር ሳይሆን ከተሳሳቱ መምህራን ከምንሰማው ነገር ነው። ከመከራ የጸዳ ሕይወት እንደሚመጣ ቃል የገባልን ይህ ቀናተኛ ሰው፣ መልእክቱን ያገኘው ከቅዱሳት መጻሕፍት ውጭ ከሆነ ምንጭ ነው።
እንዲያውም፣ መጽሐፍ ቅዱስ በመከራ ማለፋችን እንግዳ ወይም ያልተለመደ ነገር ነው ብለን እንዳናስብ ያስጠነቅቀናል። ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦
ወዳጆች ሆይ፤ እንደ እሳት የሚፈትን ብርቱ መከራ በመቀበላችሁ እንግዳ ነገር እንደ ደረሰባችሁ በመቍጠር አትደነቁ፤ ነገር ግን ክብሩ በሚገለጥበት ጊዜ ደስታችሁ ታላቅ እንዲሆን የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች በመሆናችሁ ደስ ይበላችሁ። (1ጴጥሮስ 4፥12-13)
እነዚህ ቃላት፣ ጳውሎስ በክርስቶስ መከራ “የጐደለውን መሙላት” (ቈላስይስ 1፥24) በማለት የተናገረውን ሐሳብ ያስተጋባሉ፤ ይህ በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ይበልጥ በጥልቀት የምንመለከተው፣ ትኩረት የሚስብና እውነቱን የሚያጸና ሐሳብ ነው።
ጴጥሮስ እነዚህን ቃላት ያክላል፦
ከእናንተ ማንም መከራን የሚቀበል ቢኖር፣ ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ወንጀለኛ ወይም በሰው ነገር ጣልቃ ገቢ ሆኖ መከራን አይቀበል፤ ክርስቲያን በመሆኑ መከራ ቢደርስበት ግን፣ ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር። (1ጴጥሮስ 4፥15- 16)
ወንጀለኛው በወንጀሉ ምክንያት መከራን ቢቀበል፣ ተስፋ ሊቈርጥ ይችላል፤ ነገር ግን ግራ ለመጋባት ምንም ዐይነት ምክንያት የለውም። ወንጀል የሚያስከትለው ነገር ቅጣት መሆኑ የሚደንቅ አይደለም። ከእንዲህ ዐይነቱ መከራ ጋር ኀፍረት ተጣብቆ ይገኛል።
እንደ ክርስቲያን መከራ መቀበል ምንም ዐይነት ኀፍረት የለበትም። ጴጥሮስ እንዲህ ይደመድማል፤ “ስለዚህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራ የሚቀበሉ ሁሉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ ዐደራ ሰጥተው መልካም ማድረጋቸውን ይቀጥሉ” (1ጴጥሮስ 4፥19)። እዚህ ጋር፣ ጴጥሮስ መከራ መቀበል የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጥያቄ በተመለከተ፣ ያለውን ጥርጣሬ በሙሉ አስወግዶታል። “እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ” መከራ ስለሚቀበሉት ሰዎች ይናገራል። በዚህ ክፍል፣ መከራ ራሱ የእግዚአብሔር ሉዓላዊው ፈቃድ አንዱ ክፍል ነው ማለት ነው።
በደብዳቤው ጅማሮ፣ ጴጥሮስ ስለ መከራችን ፍሬ ተናግሯል፦
አሁን በብዙ ዐይነት ፈተና ውስጥ ሆናችሁ ለጥቂት ጊዜ መከራን ብትቀበሉም እንኳ በዚህ እጅግ ደስ ይላችኋል። እነዚህ ነገሮች በእናንተ ላይ የደረሱት፣ በእሳት ተፈትኖ ቢጠራም፣ ጠፊ ከሆነው ወርቅ ይልቅ እጅግ የከበረው እምነታችሁ፣ እውነተኛ መሆኑ እንዲረጋገጥና ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን፣ ክብርንና ውዳሴን እንዲያስገኝላችሁ ነው። እርሱንም ሳታዩት ትወድዱታላችሁ፤ አሁን ባታዩትም በእርሱ ታምናላችሁ፤ መግለጽ በማይቻልና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ብሏችኋል፤ የእምነታችሁን ፍጻሜ፣ እርሱም የነፍሳችሁን ድነት እየተቀበላችሁ ነውና። (1ጴጥሮስ 1፥6-9)
ይህ ክፍለ ምንባብ ተስፋ ሳይቈርጡ ግራ መጋባት እንዴት እንደሚቻል ያሳያል። መከራችን ዐላማ አለው፤ ይህም ለእምነታችን ፍጻሜ፣ እርሱም ለነፍሳችን ድነት ይጠቅመናል። መከራ ማቅለጫ ነው። ወርቅ በእሳት እንደሚጠራ፣ ከበክሉት ቈሻሾች (dross and impurities) እንደሚነጻ ሁሉ፣ እምነታችንም በእሳት ይፈተናል። ወርቅ ይጠፋል፤ ነፍሳችን ግን አትጠፋም። ሥቃይና ሐዘን ለጊዜው ይሰማናል። በእሳቱ ውስጥ ሳለን ግራ መጋባት ያጠቃናል። ነገር ግን እሳቱ ሌላ በጎ ጎን አለው። ቈሻሻው ሲቃጠል፣ የእምነታችን እውነተኛነት እየተረጋገጠ ለነፍሳችን ድነት ይሆናል።