እውነተኛ መነቃቃት ወይም ተሐድሶ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ የሚከሰት ታላቅ ክብርን የተሞላ ወቅት ነው። በዚህም መነቃቃት ወቅት፣ እግዚአብሔር ለራሱ ክብር ብቻ ሲል በመደበኛዎቹ የጸጋ መቀበያ መንገዶች በመጠቀም፣ በብዙ ሰዎች ሕይወት ላይ የላቀና ልዩ የሆነ ተጽእኖን ያደርጋል፡፡
“የጸጋ መቀበያ መንገዶች” የሚለው ሐሳብ ቀጣዮቹን ጥያቄዎች ይመልሳል፤ እንደ አንድ አማኝ፣ እልፍ ለሆኑት መሻቶቼ የሚሆነውን የጌታን ጸጋ መቀበል የምችለው እንዴት ነው? እርሱ በዚህ ዓለም ላሉ ኀጢአተኞችና መከራ ተቀባዮች ከሚሰጠው እውነተኛ ርዳታ ለመቋደስ የምሄደው ወዴት ነው? ምንስ ነው የማደርገው? በርግጥ በጸጋው ብቻ እንደዳንኩ አምናለሁ። ግን ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ተናግሯል፤
“እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” (ማቴዎስ 11፥28-30)
ይህን አምናለሁ፤ አጥብቄም እሻለሁ። ነገር ግን በተግባር ወደ እርሱ በመምጣት የጸጋው ተካፋይ መሆን የምችለው እንዴት ነው?
የእግዚአብሔር መንገድ
በጸጋ የተሞላው ጌታችን ከእኛ ጋራ፣ “ከደረሳችሁብኝ ያዙኝ” የሚል አባሮሽ እየተጫወተ አይደለም። ይልቁንስ በእርሱ ርግጠኛ በመሆን እንድንጠጋውና ለእርሱ በሙላት ለመኖር የሚያስችለንን ኀይል ከእርሱው እንድንቀዳ ይፈልጋል። ነገር ግን እኛ ራሳችን በቀየስነው በየትኛውም መንገድ በኩል ራሱን አይገልጥልንም። እርሱ ራሱ በላቀው ጥበቡ በመረጣቸው ውስን መንገዶች በኩል ብቻ እንድናውቀውና እንድናገኘው አድርጓል። እርሱ የመረጣቸው የበረከት ጎዳናዎች፣ የጸጋ መቀበያ መንገዶች ናቸው። በዚህ ዓለም ዕለት ዕለት የምንመላለስበት መንገድ፣ ፈታኝ በሆኑ የጸጋ ፀር ጉትጎታዎች የተሞላ ነው። ነገር ግን በዚህ መንገድ ላይ ስንጓዝ ጸጋ የምንቀበልበትን ሰፊ ጎዳና ስላዘጋጀልን ጌታችን ከልብ እናመሰግነዋለን።
የዌስትሚኒስተር ካታኪዝም በጥያቄ 88 ላይ፣ “ክርስቶስ የቤዝዎቱን በረከቶች ለእኛ የሚያካፍልባቸው ውጫዊና መደበኛ መንገዶች ምንድን ናቸው?” የሚል ጥያቄን ያነሣል። ቀጥሎም ካታኪዝሙ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ፣ “ክርስቶስ ለእኛ የቤዛነት ባርኮቶችን የሚሰጥባቸው ውጫዊና መደበኛ መንገዶች እርሱ የሰጠን ሥርዐቶች ናቸው። በተለይም ቃሉ፣ ጥምቀት፣ የጌታ ራትና ጸሎት ናቸው። እነዚህ ሁሉ የተመረጡትን ለማዳን ውጤታማ በሆነ መልኩ ይሠራሉ” ይላል።
እግዚአብሔር በአስደናቂዎቹ የጸጋ ማግኛ መንገዶች ብቻ ራሱን አይገድብም። ኢየሱስ በዮሐንስ ወንጌል 3፥8 ላይ የመንፈሱ ነፋስ “ወደሚወድደው ይነፍሳል” በማለት ተናግሯል። ነገር ግን፣ “ጌታን በርግጥ ልናገኘው የምንችለው የት ነው?” ብለን ብንጠይቅ ምላሹ የሚሆነው፣ መደበኛ የጸጋ መቀበያ መንገዶች ናቸው። እነዚህም የጸጋ መቀበያ መንገዶች በጌታ ሕያው መገኘት ውጤታማ ይሆናሉ። እርሱ የመረጣቸው መንገዶች መገኘቱን ለመገደብ ያሰቡ አይደሉም። በተቃራኒው እነዚህ የመረጣቸው መንገዶች መገኘቱን በላቀ ሁኔታ የሚያትረፈርፍባቸው ስፍራዎች ናቸው። ተስፋ መቍረጥ የወረሳቸው ኀጢአተኞች ወደ ክርስቶስ ሲመጡ፣ ከዚህ ከሚፍለቀለቀው የምሕረት ፏፏቴው ይረሰርሳሉ።
የመነቃቃት መንገዶች
መነቃቃት ወይም ተሐድሶ የሚከሰተው፣ እነዚህ መደበኛ መለኮታዊ የበረከት ጅረቶች ባልተለመደ ኀይል ተትረፍርፈው ሲፈስሱ ነው። ከእኛ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ብቻ የመነጩ የወንጌል ትሩፋቶች በእኛ ላይ ተትረፍርፈው በመፍሰስ አስደናቂ ተጽእኖ ይፈጥሩብናል። አብያተ ክርስቲያኖቻችን በዚህ የወንጌል የመነቃቃት ኀይል ውስጥ እንዲያልፉ አጥብቀን የምንሻ ከሆነ፣ መፍትሔው የእግዚአብሔርን ጸጋ የምንቀበልባቸውን የራሳችንን ሥርዐቶች መፍጠር አይደለም። መፍትሔው የሚገኘው፣ ዕድሜ ጠገብ የሆኑትን የእግዚአብሔርን የጸጋ መቀበያ መንገዶችን ችላ ማለታችንን፣ እንዲሁም ያላግባብና በብልሹ መንገድ መጠቀማችንን በማረም ውስጥ ነው። እኛ የእግዚአብሔርን አሠራር ማሻሻል አይኖርብንም። ይልቁንስ ከቀድሞ በሚልቅ አክብሮትና ትሕትና ተሞልተን፣ በእግዚአብሔር አሠራር ውስጥ መሳተፍ ይኖርብናል።
የዌስትሚኒስተር ካታኪዝም ጥያቄ 85 “ከኀጢአታችን የተነሣ ከሚመጣብን የእርሱ ቁጣና ርግማን እንድናመልጥ እግዚአብሔር ምን እንድናደርግ አዞናል?” ሲል ይጠይቃል። መልሱም፦
“ከኀጢአታችን የተነሣ ከሚመጣብን የእርሱ ቁጣና ርግማን ለማምለጥ፣ እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ እንድናምንና ንስሓ እንድንገባ ይፈልግብናል። ደግሞም ከዚሁ ጋር ክርስቶስ ለእኛ የቤዛነት ባርኮቶች የሚሰጥባቸውን ሁሉንም ውጫዊና መደበኛ መንገዶችን በትጋት እንድንጠቀማቸው ያዘናል።”
እንደምናየው ካታኪዝሙ በእምነት በተሞላ ልብና በንስሓ በጌታ ፊት በመቅረብ “ውጫዊ መንገዶች በትጋት መጠቀም” እንዳለብን ብልኻት በተሞላበት ሁኔታ ያሳስበናል። ይህንም ስናደርግ ጌታ ላይ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ሳይሆን በመላው ሕይወታችን ላይ ጌትነቱን በመቀበል መሆን አለበት።
ዘኬዎስ ኢየሱስ በመንገድ ሲያልፍ እንዳያመልጠው በዛፉ ላይ በወጣ ጊዜ፣ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነገር አድርጓል። ኢየሱስ ትኩረቱን ወደ እርሱ እንዲያደርግ ማስገደድ ባይችልም፣ ራሱን በጌታ መንገድ ላይ አኑሯል። ኢየሱስ፣ ሊጎበኘው ወደደ፤ ዘኬዎስም ወደ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ተሸጋገረ። ኢየሱስም፣ “እርሱ ደግሞ የአብርሃም ልጅ ነውና ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል፤ የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአልና አለው” (ሉቃስ 19፥9-10)፡፡
የእኛ መንገድ
ነገር ግን ሁልጊዜ ጌታን በተከፈተ መንፈስ አንፈልገውም። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ጸጋውን የምንቀበልባቸውን አስደናቂ መንገዶች፣ በደካማ ሁኔታ እንጠቀማቸዋለን። በብሉይ ኪዳን የነበሩት የእግዚአብሔር ሕዝብ አምልኳቸውን አበላሽተው ነበር። እግዚአብሔር ያዘጋጃቸውን የጸጋ መቀበያ መንገዶች ልክ ሳንቲም ስንከትበት እንደሚሠራ ማሽን በመቍጠር፣ እነርሱ በሚፈልጉት ሰዋዊና “አውቶማቲክ” መንገድ እንዲሠሩላቸው ጠብቀው ነበር። ለምሳሌ፣ ኢሳይያስ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ በኦሪት ዘሌዋውያን ላይ በታዘዘው ሥርዐት መሠረት አምልኳቸውን እያቀረቡ በሙላት ቢሳተፉም, የእግዚአብሔርን ሕዝብ አምልኮ አውግዞታል። እግዚአብሔርም በኢሳይያስ በኩል፣ “እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ ዐይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፥ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል” ይላቸዋል (ኢሳይያስ 1፥15)።
የእግዚአብሔር ሕዝብ የእግዚአብሔርን የጸጋ መቀበያ መንገዶች ያላግባብ እየተጠቀሟቸው ነበር። እግዚአብሔርም ሊቀበላቸው አልወደደም። ለመሆኑ ጌታን በዚህ መጠን ያስቈጡት ምን ቢያደርጉ ነው? በርግጥ ተከፋፍለው ነበር። አንዳቸው ለአንዳቸው ጨካኝ ከመሆናቸውም ባለፈ፣ እጆቻቸው በሰው ደም ያደፉ ነበሩ። ወዲያውም አሳዛኙን ምጸት ሳይረዱ፣ ለአምልኮ ወደ መቅደሱ በመሄድ ደም ያፈሰሱባቸውን እጆች በእግዚአብሔር ፊት ለጸሎት ያነሧቸው ነበር። እግዚአብሔር ግን ይህን ዐይቶ ነበር። ያልተፈተነ ሕይወታቸው ባርኮቱን ለመቀበል ዝግጁ አለመሆኑን ተናገረ። ሕዝቡ በሕይወታቸው ሙሉ ወደ መታዘዝ ሙላት ለመድረስ ከመትጋት ይልቅ የእግዚአብሔርን የጸጋ መቀበያ መንገዶች ከከበረው ታዛዥነት ለመሸሽ ተጠቅመውባቸዋል።
በአዲስ ኪዳን ያለውም የእግዚአብሔር ሕዝብ፣ የጸጋ መቀበያ መንገዶችን ያላግባብ ሲጠቀም እናያለን። በቆሮንቶስ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን አባላት የጌታን ራት “ሳይገባቸው” ይወስዱ ነበር (1 ቆሮንቶስ 11፥27)። ይህም፣ በዚህ ቅዱስ በሆነው አንዱ ሥርዐት የሚታወጀውን፣ የክርስቶስን ፍቅር በሚፃረር መልኩ በትዕቢት ተሞልተውና ተከፋፍለው ነበር ማለት ነው። ራስ ወዳድነታቸው፣ ይህን ቅዱስ ስጦታውን ያላግባብ እንዲጠቀሙበት ስላደረገ፣ በተቃራኒው የፍርድ ምክንያት ሆኖባቸዋል።
“ምክንያቱም ማንም የጌታን ሥጋ ሳይገባው ቢበላና ቢጠጣ ፍርድ የሚያመጣበትን ይበላል፤ ይጠጣልም፡፡ ስለዚህ ከእናንተ መካከል ብዙዎች የደከሙትና የታመሙት፣ አንዳንዶችም ያንቀላፉት በዚህ ምክንያት ነው” (1 ቆሮንቶስ 11፥29-30)።
እነዚህን የጸጋ መቀበያ መንገዶች በሰዋዊ መንገድ እንደሚሠሩ አስበን ልንቈጣጠራቸው ከሞከርን፣ እግዚአብሔር ያዝናል። ነገር ግን ሙሉ መገኘታችንን ወደ እግዚአብሔር ግልጽ ህልውና ካስጠጋን፣ ጌታ በሙሉ ደስታ በጸጋ መቀበያ መንገዶቹ አማካይነት ልባችንን ይባርካል።
ትሕትናና እውነተኛነት
ጌታ ባዘጋጃቸው መንገዶች በኩል በትሑት እምነትና ወደ ወንጌል ጥሪ በሚያደርስ እውነተኛ ንስሓ ወደ እርሱ ስንቀርብ ምንኛ ታላቅ መነቃቃት ይሆናል! የጥንቷም ቤተ ክርስቲያን እነዚህ የእግዚአብሔር መንገዶች ላላቸው ኀይል ሕያው ማሳያ ነበረች።
“በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር … እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ በሕዝብ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው። ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር” (የሐዋርያት ሥራ 2፥42)፡፡
ከጥንቷ ቤተ ክርስቲያን አስደናቂ ነገሮች አንዱ፣ የሕይወት ዘይቤያቸው እጅግ ቀላልና በዚያውም ልክ ተጽእኖ ፈጣሪ የነበረ መሆኑ ነው። ይህን እኛ ልንረዳው የምንችለው እንዴት ነው? የጆናታን ኤድዋርድን አገላለጽ እዚህ ጋር ብንጠቀም፣ እነዚህ የጥንት ክርስቲያኖች ራሳቸውን “በማራኪው መንገድ ላይ” ያኖሩ ነበር። ማለትም፣ ክርስቶስ ተስፋ አድርጎ በሰጠው የኀይል ጎዳና ላይ ራሳቸውን በደስታ ያስቀምጡ ነበር። በርግጥም የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ማበቧ አያስገርምም።
በአንድ የመንፈሳዊ መነቃቃት ወቅት በስኮትላንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አገልጋይ የነበረው ቻርለስ ጄ ብራውን፣ በጊዜው በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የነበረውን የእግዚአብሔርን ጸጋ ኀይል በዐይን እማኝነት እንዲህ ብሎ ጠቅሶ ነበር፡-
“ከመደበኛው አገልግሎት በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ተከፍቶ አንባቢው ንባቡን በጀመረበት ቅጽበት በሰሚዎቹ ላይ ታላቅ መራድ መከሰቱ የተለመደ ነገር ነበር። የተቀደሱት ጥቅሶች በዝግታና በክብር ሲነበቡ፣ ለእያንዳንዱ ቃል ጥልቅ ትኩረት ይሰጥ ነበር። ቀጥሎም በዝምታ የታጀበ የእንባ ዘለላ ኮለል ብሎ እየወረደ የሰሚዎቹን ፊት ሲያረሰርስ ይታይ ነበር። ግርምት የሞላቸው የፊት ገጽታዎችም ትክ ብለው አንባቢውን ይመለከቱት ነበር። በእነዚህ ቀናት የጌታ ቃል እጅግ የከበረ ነበር።”
ከዚህ እንደምናየው በሰዎቹ ልብ ውስጥ የነበረው ኀይል የተከሰተው፣ በስብከት ሳይሆን እንዲያው በቃሉ ንባብ ብቻ ነበር። በርግጥም እግዚአብሔር ባዘጋጃቸው የወንጌሉ ጸጋ መቀበያ መንገዶች ውስጥ የሚያነቃቃ ኀይል አለ። ከዚህስ ሌላ ምን ያሻናል?